በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከህወሓት ታጣቂዎች የቡድን መሳሪያ ተረከበ - ኢዜአ አማርኛ
በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከህወሓት ታጣቂዎች የቡድን መሳሪያ ተረከበ
አዲስ አበባ ግንቦት 18 /2015 (ኢዜአ)፡- በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከህወሓት ታጣቂ ሃይሎች የቡድን መሳሪያ ተረከበ፡፡
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ከዚህ ቀደም የከባድ መሳሪያ ርክክብ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን፤ በወቅቱ የከባድ መሳሪያ ርክክቡ መገለጹ ይታወሳል፡፡
ዛሬ የተደረገው ርክክብም የዚሁ ስራ አካል መሆኑ ነው የተጠቆመው፡፡
ርክክቡ በመቀሌ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ልዩ ቦታው ላጪ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተካሄደ ሲሆን፤ በርክክብ መርሃ ግብሩ የአፍሪካ ህብረት ታዛቢዎች ተገኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ተወካይ ብርጋዴር ጀነራል ደርቤ መኩሪያ እንደገለጹት የመሳሪያ ርክክቡ የሰላም ስምምነቱ አንድ አካል ነው።
በርክክቡም የቡድን መካከለኛ መሳሪያ የሚባሉ የጦር መሳሪያዎችን መረከባቸውን ገልጸዋል።
የህወሓት ታጣቂ ኃይሎች ተወካይ ብርጋዴር ጀነራል ምግበይ ኃይለ በበኩላቸው የቡድን መሣሪያ ርክክቡ በሰላም ስምምነቱ መሰረት መፈጸሙን ገልጸው፤ ለሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚነት የበኩላቸውን በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሰላም የመጀመሪያ እና የመጨረሻ ግባቸው መሆኑን በመጠቆም።
ርክክቡን የታዘቡት የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ እና አረካካቢ ኮሚቴ አባል ብርጋዴር ጀነራል ቴፎ ሶኮሌ ርክክቡ የሰላም ስምምነቱ በጥሩ ሁኔታ እየተፈጸመ ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።