ኢትዮጵያ በችግር ውስጥ ያሉ አገራትን ባላት አቅም ለማገዝ የምታደርገው ጥረት ከጥንት ጀምሮ የምትታወቅበት መገለጫዋ ነው-ኮሚሽነር ሺፈራው

183

አዲስ አበባ ግንቦት 18/2015 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በችግር ውስጥ ያሉ አገራትን ባላት አቅም ለማገዝ የምታደርገው ጥረት ከጥንት ጀምሮ የምትታወቅበት መገለጫዋ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን  ኮሚሽነር ዶክተር ሺፈራው ተክለማርያም ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ''ጦርነት ይብቃ፤ ሰላምን እናጽና'' በሚል ሚያዚያ 15 ቀን 2015 ዓ.ም በወዳጅነት አደባባይ በተዘጋጀው መርሀ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ሌሎች ሀገራት በተቸገሩ ጊዜ ኢትዮጵያን በመርዳት ትታወቃለች ሲሉ ተናግረዋል።

በሰላም ማስከበር ተልዕኮና ለሰላም ዘብ በመቆም ስሟ የሚጠቀሰው ኢትዮጵያ ተርክዬ በርዕደ መሬት በተመታች ጊዜ የነፍስ አድን ቡድንና ሰብዓዊ ድጋፍ በመላክ ከጎኗ መሆኗን ማሳየቷ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ሰብአዊ ተግባሯን በመቀጠል በችግር ውስጥ ላለችው ሱዳንም "ኢትዮጵያን ኤይድ" በሚል የ50 ሺህ ኩንታል ስንዴና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለፃቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ሌሎች አገራትን ባላት አቅም ለማገዝ የምታደርገው ጥረት ከጥንት ጀምሮ እያደረገችው የዘለቀችበትና  የምትታወቅበት ታሪኳ  መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሺፈራው ተክለማርያም ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በጦርነትና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ለተጎዱ ሀገራት ወታደሮቿንና ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎችን በማድረግ ኢትዮጵያ የገዘፈ ታሪክ ያላት መሆኑን አንስተዋል።

"በዛሬው የኢኮኖሚ አቅም ላይ ባልሆንበት ወቅቶችም ለተቸገሩ ደራሽ በመሆን በዓለም ደረጃ የምንታወቅበት ጊዜም ነበር" ብለዋል።

ከምግብና ደራሽ ድጋፎች ባሻገር ሀገራት ሉዓላዊነታችን ተደፈረ ባሉ ጊዜ ዓለም አቀፋዊ ሚናዋን ስትወጣ ሀገራትን ስታግዝ ቆይታለች ብለዋል ኮሚሽነሩ።

ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ሰው ሰራሸና የተፈጥሮ ችግሮች በመቋቋም ጎረቤት አገር ሱዳንን ለማገዝ እጇን መዘርጋቷ የምንጊዜም አጋር መሆኗን በተግባር ያሳየችበት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ለቱርክዬ ባደረገችው ድጋፍና አብሮነት ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ምስጋና በማቅረብ አድናቆታቸውን መግለፃቸውም ሌላኛው ማሳያ መሆኑን ዶክተር ሽፈራው ጠቅሰዋል።

በዓለም ታሪክ የትኛውም አካባቢ ልኩና ደረጃው ቢለያይም ተረጂ የሌለበት ሀገር የለም ያሉት ኮሚሽነሩ፤ አውሮፓና አሜሪካም ቢሆኑ በማህበራዊ ዋስትና ስም የሚደጉሟቸው ተረጂ ዜጎች እያሏቸው ሌሎችን ሀገራት የሚያግዙ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያም በቻለችው ሁሉ የምታደርጋቸው የሰብዓዊ ድጋፎችም ታሪካዊ በጎ ስሟን የሚያጸና እና ስሟን በዓለም አደባባይ ከፍ አደርጎ የሚያስጠራ መሆኑን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም