በበጀት ዓመቱ 10 ወራት ለ 1 ሺህ 458 ድርጅቶች የታክስ ቅሬታ ውሳኔ ተሰጥቷል- የገቢዎች ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ግንቦት 18/2015 (ኢዜአ)፦በ2015 በጀት ዓመት 10 ወራት ለ 1 ሺህ 458 ድርጅቶች የታክስ ቅሬታ ውሳኔ መሰጠቱን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።

የቅሬታ ምንጭ የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት የሕግና የአሰራር ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑንም ገልጿል።

የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ውሳኔ ቅሬታ አጣሪ ጽህፈት ቤት የታክስ መሪ ባለሙያ ወይዘሮ ፀሐይ ሀብቴ በበጀት ዓመቱ 10 ወራት ከ2014 በጀት ዓመት የዞሩ 64 ፋይሎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 1 ሺህ 553 ድርጅቶች በብር ከ26 ቢሊዮን 37 ሚሊዮን ብር በላይ የታክስ ውሳኔ ቅሬታ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።


 

ከነዚህ ውስጥ ለ1 ሺህ 458 ድርጅቶች በብር 23 ቢሊዮን 187 ሚሊዮን 255 ሺህ 257 ውሳኔ መሰጠቱን አመልክተዋል።

95 ድርጅቶች በብር 2 ቢሊዮን 850 ሺህ 479 ያቀረቡት የታክስ ውሳኔ ቅሬታ ወደ ግንቦት 2015 መዞሩንም ጠቁመዋል።

ከውሳኔው በተጨማሪ በተደጋጋሚ የቅሬታ ምንጭ የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት የሕግና የአሰራር ማሻሻያ የማድረግ እንዲሁም ስልጠናዎች የመስጠትና የክትትልና ድጋፍ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ መግለጻቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም