የዋንጫ ተፎካካሪዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስና ባህር ዳር ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው

153

አዲስ አበባ ግንቦት 18/2015 (ኢዜአ):-በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ተከታዩ ባህር ዳር ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ በእግር ኳስ አፍቃሪው ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል።

በሊጉ የዋንጫ ፉክክር ወሳኝ የሆነው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 12 ሰአት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋል።

በደረጃ ሰንጠረዡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ55 ነጥብ 1ኛ ሲሆን ባህር ዳር ከተማ በ50 ነጥብ 2ኛ ደረጃን ይዟል።

በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚሰለጥነው ቅዱስ ጊዮርጊስ እስከ አሁን በፕሪሚየር ሊጉ ካደረጋቸው 25 ጨዋታዎች 16ቱን ሲያሸንፍ 2 ጊዜ ተሸንፏል፤ 7 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።

በ25ቱ ጨዋታዎች ፈረሰኞቹ 46 ግብ ሲያስቆጥሩ 16 ጎሎችን አስተናግደዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች በሶስቱ አሸንፎ በአንድ ተሸንፎ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።

በአሰልጣኝ ደግ አረገ ይግዛው የሚመራው ባህር ዳር ከተማ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 25 ጨዋታዎች 14ቱን ሲያሸንፍ በሶስቱ ተሸንፏል፤ 8 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።


 

የጣና ሞገዶቹ በ25ቱ ጨዋታዎች 44 ጎሎችን ሲያስቆጥሩ 22 ግቦችን አስተናግደዋል።

ባህር ዳር ከተማ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ ሁለቱን ተሸንፎ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ከተከታዩ ባህር ዳር ከተማ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ስምንት ከፍ በማድረግ 16ኛውን የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ ለማንሳት ይበልጥ ይቀርባል።

በአንጻሩ ባህር ዳር ከተማ በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ የሚጠበቅበት ሲሆን ጨዋታውን ካሸነፈ ከፈረሰኞቹ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ ያደርጋሉ።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር በ10ኛ ሳምንት በድሬዳዋ ስታዲየም ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

ከሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ቀደም ብሎ የ26ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ከፕሪሚየር ሊጉ መውረዱን ባረጋገጠው ለገጣፎ ለገዳዲ እና አዳማ ከተማ መካከል ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይደረጋል።

በደረጃ ሰንጠረዡ ለገጣፎ ለገዳዲ በ12 ነጥብ 16ኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን አዳማ ከተማ በ33 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ አዳማ ከተማ 3 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል።

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት መርሐ- ግብር እስከ ግንቦት 21/ 2015 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም