በካምፓላ ኢትዮጵያ ኤምባሲ የአፍሪካ ቀን ልዩ አከባበር ተካሄደ

204

 

አዲስ አበባ ግንቦት 18/2015(ኢዜአ):-በካምፓላ ኢትዮጵያ ኤምባሲ ፓን-አፍሪካኒዝምን ከማጠናከር አኳያ የአፍሪካ ቀን ልዩ አከባበር ተካሔደ።

ከኢትዮጵያውያን የኮሚኒቲ ማህበር፣ ከሌሎች በዩጋንዳ ተቀማጭ የሆኑ የአፍሪካ አገራት ኤምባሲዎችና ከፍተኛ ኮሚሽነሮች እንዲሁም የዩጋንዳ መንግስታዊና መንግስታዊ-ያልሆኑ ተቋማት ጋር “የአፍሪካ ቀን” የአፍሪካ ህብረት 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በካምፓላ ኤር-ስትሪፕ አደባባይ በደማቅ ስነ-ስርዓት ተከብሯል፡፡

በዓሉ ከዩጋንዳ የነጻነት አደባባይ እስከ ኤር-ስትሪፕ አደባባይ በማርሽ ባንድ የታጀበ የእግር ጉዞ(ሰልፍ) የተደረገ ሲሆን በዚህ የአንድ ሰዓት የእግር ጎዞ በሰንደቅ ዓላማ እና በባህላዊ አልባሳት የታጀበው የኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበረም ተገልጿል።

በዝግጅቱ ላይ በካምፓላ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኮሚኒቲ እና በካምፓላ ከሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር ደማቅ አከባበር የተደረገ ሲሆን፣ አምባሳደር እፀገነት በዛብህ ይመኑ እና የሚሲዩኑ ዲፕሎማቶችና ቤተሰቦቻቸውም ታድመዋል።

በዚህም ከባህላዊ አልባሳት ጀምሮ የኢትዮጵያን ባህል፣ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች እና መዳረሻዎች የማስተዋወቅ ስራም ተከናውኗል።

ከ100 በላይ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላትና የኤምባሲው ባልደረቦች የቡና ስነ ስርዓት እና ባህላዊ ምግቦችን በማቅረብ የኢትዮጵያን ደማቅ ባህልና ወግ አሳይተዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያን ልዩ የአማርኛ ፊደላት ጎብኚዎች ስማቸውን በፊደላት እንዲጽፉ በማድረግ የማለማመድ ተግባር በአዝናኝ ሁኔታ የማስተዋወቅ ስራ ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ዝግጅት ላይ በልዩ ሁኔታ የዩጋንዳ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሮቢናህ ናባንጃ ፣ በዩጋንዳ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ዲን ፣ የተለያዩ ሃገራት ሚሲዮን ኃላፊ አምባሳደሮችና ኮሚሽነሮችና የዩጋንዳ የመንግስትና የግል ድርጅቶች ከፍተኛ ባለስልጣናትና ሌሎችም መገኘታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ሽፋን በተሰጠው በዚህ ዝግጅት ላይ “ጉርሻ ከአገልግል” በሚል ኢትዮጵያዊ ወግን በማሳየት ከአንድ ማዕድ ተጋርቶ መብላት እና ጉርሻ መቀበል የታዳሚያንን ቀልብ የሳበ እንደነበረም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም