የቤንች ሸኮ ዞን ለትግራይ ክልል መልሶ ማቋቋም ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ ድጋፍ አደረገ

ሚዛን አማን ግንቦት 17/2015  (ኢዜአ) የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳደር ለትግራይ ክልል መልሶ ማቋቋም የሚሆን ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ፡፡

የቤንች ሸኮ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ሲቪል ማህበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ምትኩ መሀመድ በዛሬው ዕለት ሰብዓዊ ድጋፉን የጫኑ ተሽከርካሪዎች ድጋፉን ይዘው ወደ ክልሉ ጉዞ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በድጋፉ የስንዴ ዱቄት፣ በቆሎ፣ ባቄላ እና ማሽላ መካተታቸውንና ግምታዊ ዋጋቸውም ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ድጋፉ በዞኑ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችንና በዞኑ ያሉ ሁሉንም መዋቅሮች በማሳተፍ በተገኘ ገንዘብና ለመጀመሪያ ዙር የተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

በትግራይ ክልል በጦርነት ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች ለተጋለጡ ዜጎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ያለመ እንደሆነም ነው አቶ ምትኩ የጠቆሙት።

የዞኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽመልስ መኩሪያ በበኩላቸው እንዳሉት በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚደረገው ሰብአዊ ድጋፍ ቀጣይነት እንዲኖረው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።

ለትግራይ ክልል በተደረገው የድጋፍ ማሰባሰብ ሥራ የተሳተፉ የዞኑ ማህበረሰብ እና ሌሎች አካላት ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም