በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ጫና ለመፍጠር የሚደረጉ ሙከራዎችን ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር መመከት ይገባል-ምሁራን

265

ሶዶ ግንቦት 17/2015 (ኢዜአ) በታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ጫና ለመፍጠር የሚደረጉ ሙከራዎችን ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር መመከት እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ጋር የተያያዙ ያልተገባ ጫና ለመፍጠር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ውስጣዊ አንድነት በማጠናከር መመከት እንደሚገባ ምሁራኑ ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ የተፋሰሱ አገሮችን ትብብር በማጠናከር ''ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ'' በሚል መርህ ብቻ ለመፈታት እየተደረገ ያለው ጥረትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል።

ዶክተር አበሻ ሽርኮ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ናቸው።

እሳቸው እንዳሉት ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን በበለጠ አጠናክረው ያልተገቡ ውጫዊ ጫናዎችን በመቋቋም በራሳቸው ተሳትፎ የጀመሩትን ግድብ ከዳር ለማድረስ በበለጠ መትጋት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።

የዓለም አቀፍ መርህ ተከትሎ እየተገነባ ያለው የህዳሴ ግድብ የታችኞቹ የተፋሰስ አገሮችን የውሃ መጠን ስለማይቀንሰው ስጋት ሊሆን እንደማይገባ ምሁሩ ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ የመጠቀም መብቷ ማንም ሊነካው የማይችል መሆኑን መረዳት ያስፈልጋልም  ብለዋል። 

የዓረብ ሊግ አባል አገሮች ሰሞኑን ያወጡት መግለጫ ዓለም አቀፉን ድንበር ተሻጋሪ የውሃ  አጠቃቀም ሕግ የሚፃረርና ሚዛናዊነት የጎደለው መሆኑንም ተናግረዋል። 

ሊጉ የግድቡን ግንባታና ሌሎች ሥራዎችን ለሚመለከታቸው አካላት ሊተው እንደሚገባ ያመለከቱት ምሁር፣ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች "ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ" መርህ መሠረት መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ጳውሎስ ባልቻ አገሮች የሚጋሩትን ወንዝ ፍትሐዊና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የመጠቀም እኩል መብት እንዳላቸው አስረድተዋል። 


 

ኢትዮጵያም መርሁን ተከትላ የተፈጥሮ ሀብቷን በዓለም አቀፉ ድንበር ተሻጋሪ የውሃ አጠቃቀም መርህ መሠረት ፍትሃዊና ሚዛናዊ የአጠቃቀም መርህ በመከተል ተጠቃሚነቷን ልታረጋግጥ እንደሚገባ ተናግረዋል። 

በዓባይ ወንዝ ያላትን ተጠቃሚነትም ተጋሪ አገሮችን በማይጎዳ መልኩ ጥቅም ላይ እያዋለች መሆኗን ገልጸዋል። 

የግድቡ ኃይል ማመንጨት ከተፋሰሱ አገሮችጋር ቀጣናዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን የሚያጠናክር እንጂ ፤ጉዳት የማያደርስ መሆኑ መዘንጋት የለበትም ብለዋል። 

የዓረብ ሊግ በግድቡ ግንባታ ሂደት ከመርህ ውጭ በሆነ መልኩ ሰሞኑን ያወጡት መግለጫ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል። 

በተለይም የህዳሴ ግድብ አራተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መቃረቡን ተከትሎ የተለያዩ ጫናዎች እንደሚጠበቁ በማመላከት።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም