የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የምታደርገውን ጉዞ እውን ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጾ እያደረገ ነው--አቶ መላኩ አለበል

79

ባህር ዳር ግንቦት 17/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪውን እንቅስቃሴ ከማፋጠን ባለፈ ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የምታደርገውን ጉዞ እውን ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገለፁ።

ንቅናቄው በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ቅንጅታዊ ሥራን ከማሻሻል ባለፈ በርካታ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ማስቻሉንም ገልጸዋል።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 11ኛው ዓለም አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ እያካሄደ ነው።

በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት ሚኒስትሩ እንዳሉት በ"ኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ በሃገር ውስጥ ያሉ እድሎችን አቀናጅቶ በመጠቀም ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ እየተሰራ ነው።

መንግስት የሃገር ውስጥ ምርታማነትን ለማሳደግ ዘርፍ ብዙ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣  በተለይም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሃገር ውስጥ አቅሞችን አቀናጅቶ በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።

በንቅናቄው ለ10 ዓመታት ግብ ተጥሎ ሥራ ቢጀመርም ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ ግቡን መሳካት እንደሚቻል ያሳየ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል ሚኒስትሩ።

ንቅናቄው የኢንዱስትሪውን እንቅስቃሴ ለማፋጠንና ሀገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር የጀመረችውን ጉዞ እያፋጠነ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

አቶ መላኩ እንዳሉት ንቅናቄው ከተጀመረ ወዲህ በተፈጠረ ግንዛቤ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ቅንጅታዊ ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ ከመሻሻሉ ባለፈ በርካታ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል።

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካትና ወጪ ምርቶችን በማሳደግ በኩልም  ሚና እየተጫወተ መሆኑን ያስረዱት።

የኢትዮጵያ ታምርት በፓሊሲና ስትራቴጂ ተደግፎ እየተሰራ መሆኑን አቶ መላኩ ገልጸው፣ "ይህም የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በማጎልበት ተወዳዳሪነታቸውን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ያስችላል" ብለዋል።

ይህን ለማሳካት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በኢንዱስትሪዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን በጥናትና ምርምር ለይቶ ለመፍትሄው እያደረገ ላለው አስተዋጾም ሚኒስትሩ አመስግነዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የተመሰረተበትን 60ኛ ዓመት በተለያዩ እንቅስቃሴዎች እያከበረ መሆኑን ገልጸዋል።

ተቋሙ ችግር ፈች የምርምር ስራዎችን በማከናወን ግንባር ቀደም ሆኖ ለመገኘት የሚያስችለውን ግብ ጥሎ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ "የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ኢንስቲትዩት እያደረገው ያለው ጥረትም የዚሁ አካል ነው" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እውን እንዲሆን የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ለዚህም ዩኒቨርሲቲው በትብብር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

"ኢንስቲትዩቱ በጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ በፋሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የበቃ የሰው ሃይል በማፍራት ለሃገሪቱ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው" ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶክተር ታምራት ተስፋዬ ናቸው።

በአካባቢው ያሉ ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን ችግሮች በመለየት ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ውጤታማ እንዲሆን ምሁራን ሚናቸውን እንዲወጡ ለማስቻል የጥናትና ምርምር ኮንፈረንሱ መዘጋጀቱንም ዶክተር ታምራት አስታውቀዋል።

ኢንስቲዩቱ ባዘጋጀው በእዚህ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ 30 የምርምር ሥራዎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ታውቋል።

ከእዚህ በተጨማሪ ባዛር፣ ፋሽን ሾዎ እና ሌሎች ሁነቶች መዘጋጀታቸውን ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም