በአፋር ክልል የስራ ዕድል ፈጠራ ማሳደግ እና የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው--የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች

92

ሠመራ ግንቦት 17/2015 (ኢዜአ)፦በአፋር ክልል የስራ ዕድል ፈጠራ እና የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች አስታወቁ።

በክልሉ ''የመንግሰት ቅቡልነት ምንነት፣ ማረጋገጫ መንገዶች እና የብልፅግና አቅጣጫዎች'' በሚል መሪ ሃሳብ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የውይይት መድረክ ተጠናቋል።

በዚሁ ወቅት ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በክልሉ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ድህነት ቅነሣ ላይ ያተኮረ ስራ እየተከናወነ ነው።

ከአመራሮቹ መካከል የብልፅግና ፖርቲ የአፋር ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢሴ አደን ኢሴ እንዳሉት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ግብርና በስፋት ይከናወናል ሲሉ ገልጸዋል።

በክልሉ ባለፉት ጥቂት አመታት የተጀመረው የግብርና ልማት ስራ ትልቅ ውጤት የተገኘበት መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ይህው ጅምር ስራ ይጠናከራል ብለዋል።

አቶ ኢሴ እንደተናገሩት ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ስርዓት በማስያዝ፤ ነጋዴው በትክክለኛ መንገድ የንግድ ስራውን እንዲያከናውን ቁጥጥር ይደረጋል ።

የአፋር ክልል የስራ እና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መይረም ወለይሰም፤ የስራ ዕድል ፈጠራ ለማስፋፋት እና የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት በቀጣይነት በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን በሕዝቡ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ ስራዎች የሚከናወኑ ይሆናልም ነው ያሉት።

የአፋር ክልል ንግድ፣ ገበያ ልማት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ መሃመድ ሁመድ በበኩላቸው ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ በሁሉም ዘርፎች ትኩረት በማድረግ በቀጣይነት ይሰራል ብለዋል።

አቶ መሃመድ እንደገለፁት በክልል ደረጃ በተያዘው እቅድ መሰረት የስራ ዕድል ሲፈጠር ምርታማነት እያደገ የኑሮው ውድነቱም እየቀለለ ይመጣል።

የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሸን አገልግሎት ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሐዋ አሊም እንዲሁ እንደ ክልል ባለፈው ዓመት የነበረውን የምርት ማሳደግ ተሞክሮ የበለጠ በማሳደግ ይሰራል ብለዋል።

በአፋር ክልል በሚገኙ ማሳዎች የተለያዮ አትክልቶች እና ፍራፍሬዎች ተመርተው ከአካባቢው አልፎ ለተለያዮ ከተሞች ለገበያ መቅረባቸውን አስታውሰዋል።

ትናንትና የተጀመረው የውይይት መድረክ በዛሬው ዕለት የተጠናቀቀ ሲሆን እስከ ታች ድረስ የንቅናቄ ስራዎች እንደሚሰራ በመድረኩ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም