ኢጋድ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በወንጀል ፍትህ ስርዓት ላይ ተናበው እንዲሰሩ በማድረግ በቀጠናው ዘላቂ ሠላምና ዴሞክራሲን ለማስፈን እየሰራ ነው

135

ሀዋሳ ግንቦት 17/2015 (ኢዜአ)  የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ላይ ተናበው እንዲሰሩ በማድረግ  በቀጠናው ዘላቂ ሠላምና ዴሞክራሲ ለማስፈን እየተሰራ መሆኑን  የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት  “ኢጋድ ” ዋና ፀሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ገለጹ ፡፡

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት “ኢጋድ” አባል ሀገራት በወንጀል ፍትሕ ሥርዓትና በሽብር ወንጀሎች ላይ ያተኮረ የምክክርና የልምድ ልውውጥ መድረክ በሻሸመኔ ከተማ እያካሄዱ ነው፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት “ኢጋድ” ዋና ፀሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ላይ ተናበው እንዲሰሩ በማድረግ በቀጠናው ዘላቂ ሠላምና ዴሞክራሲን ለማስፈን ኢጋድ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

መድረኩ በአባል ሀገራቱ መካከል ያለውን የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት አተገባበርና ተሞክሮ ማካፈልን እንዲሁም ተቀራራቢ የወንጀል ፍትሕ እንዲኖር የሚያስችል የእውቀትና የአቅም ግንባታ ሥራ መስራትን ዓላማው ያደረገ እንደሆነም ገልጸዋል ፡፡

ይህም አባል ሀገራቱ በሽብር ተግባራት በተለይም በድንበር ዘለል ወንጀሎች ላይ ተቀራርበው እንዲሰሩና ለወንጀለኞች የማይመች ቀጠና በመፍጠር በአካባቢው ሠላምና የሕግ የበላይነትን ማስፈን የሚያስችላቸው መሆኑንም አስረድተዋል ፡፡

የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት በዋናነት ከዜጎች ነፃነት ጋር እንደሚያያዝ ጠቅሰው፤ በዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት በአባል ሀገራት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ የሚኖረው አዎንታዊ ተፅዕኖው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

ኢጋድ በምሥራቅ አፍሪካ ላይ በፀጥታና ደህንነት፣ በቀጠናዊ የንግድ ትስስር መዳበር፣ ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በመከላከል፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በዜጎች ድንበር ዘለል እንቅስቃሴዎችና በሌሎች ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ሀገሮችን የማገዝ ስራ እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

እንዲሁም ተባብሮ የመስራት ባህል እንዲዳብር በማጠናከርና ፖሊሲዎችን የማውጣትና የማስተግበር ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡

ከተሳታፊዎች መካከል በኡጋንዳ የሽብር ወንጀል መከላከል ዳይሬክተር ውስጥ የፖሊስ መኮንን የሆኑት አንሴሌ ሙጂሻ መድረኩ በአገራቸው ያለውን ተሞክሮ እና የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች በተመለከተ መረጃ ለመለዋወጥ የሚጠቅም ነው ብለዋል ፡፡


 

በተለይ የሽብር ወንጀሎችን በመከላከል ውስጥ የፍትሕ አካላት ተናበው መሥራት አለባቸው ያሉት የፖሊስ መኮንኑ መድረኩ ለዚህ ሥራ ምቹ መደላድል የሚፈጥር ነው ብለዋል ፡፡

ሀገራት በተቀናጀ መንገድ የሚያከናወኑት ተግባር ወንጀልን ከመከላከል አንጻር ተስፋ ሰጪ ውጤት እየታየበት መሆኑን ኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ዘርፍ በተደራጁና ድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች ጉዳይ በዐቃቤ ሕግነት የሚያገለግሉት አቶ ቃሲም አማን ገልጸዋል፡፡

እንደ ሀገር የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና የሚያስከትለውን አስከፊ ጉዳት ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀው ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከወንጀሉ ባህሪና አኳያ በቂ ሥራዎች ያልተሰሩ በመሆኑ ከኢጋድ እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር የበለጠ ቁርኝት በመፍጠር መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል ፡፡

በመድረኩ ከስምንቱ የኢጋድ አባል ሀገራት እንዲሁም ከታንዛንያና ሩዋንዳ የመጡ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ባለድርሻ የሆኑ ዳኞች፣ ዐቃቤ ሕጎች፣ መርማሪ ፖሊሶች የተገኙ ሲሆን፤መድረኩ ለቀጣይ ሁለት ቀናት እንደሚካሄድ ከወጣው መርሃ ግብር ማወቅ ተችሏል ፡፡

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም