ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር የህዝብን ጥያቄዎች ለመመለስና ለውጡን ለማስቀጠል አንድነትን ማጠንከር እንደሚገባ ተገለጸ

173

ጎንደር/ መተማና/ ሰቆጣ ግንቦት 17/2015  (ኢዜአ) ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር የህዝብን ጥያቄዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመመለስና ለውጥን ለማስቀጠል ከምንግዜም በላይ ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።

በየደረጃው አመራሩ ብልሹ አሰራርና ጽንፈኝነትን በቁርጠኝነት በመታገል ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግ እንዳለበትም ተመላክቷል።

"ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር ህዝባችንን እናሻግራለን" በሚል መሪ ሃሳብ በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች እንዲሁም ዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ድርጅታዊ ኮንፍረንስ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።

የአማራ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃኑ ጣምያለው በጎንደር ከተማ በተጀመረው ኮንፈረንስ ላይ ተገኝተው እንዳሉት ህዝብን ወደሚፈለገው ደረጃ ለማሻገር ከሁሉም በላይ አንድነትን ማጠንከር ይገባል። 

"ጠንካራ መዋቅር ከሌለ ህዝብን ለማሻገር አይችልም" ያሉት አቶ ብርሀኑ፣ የፓርቲ አመራሮች የህዝብን ችግር ለመፍታትና ወደተሻለ ደረጃ ለማሻገር በተግባር አንድ መሆን መሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።

"እንደ ሀገር ከብልጽግና ፓርቲ መመስረት በኋላ የመጡ ድሎች በቀጣይ ሰፍተውና ህዝባዊ መሰረት ይዘው እንዲቀጥሉ በየደረጃው ያለን አመራሮች አስፈላጊውን መስዋዕትነት መክፈልና በጋራ መቆም ይገባናል" ብለዋል።

የለውጥ ጉዞ ብዙ ውጣ ውረዶች የበዙበትና ፈተናውም ከባድ በመሆኑ ለውጡን ለማስቀጠል ጸንቶ መታገል ይጠይቃል ያሉት ደግሞ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ሃይለማርያም ናቸው።

አሁን እየገጠሙ ያሉ ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር ለውጡን ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ለእዚህም ከምንግዜው በላይ ውስጣዊ አንድነታችንን ማጠናከር ያስፈልጋል" ብለዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የብልጽግና ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፈንታሁን ስጦታው በበኩላቸው "ኮንፈረንሱ በለውጡ ሂደት የተገኙ ድሎችን ለማጽናትና ለችግሮች የጋራ መፍትሄ ለማስቀመጥ ጠቀሜታው የጎላ ነው" ብለዋል።


 

በተመሳሳይ ዜና በምዕራብ ጎንደር ዞን መካሄድ በጀመረው ኮንፈረንስ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ እርዚቅ ኢሳ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ሀገራዊና ህዝባዊ አንድነትን ለማጠናከር አመራሩ ብልሹ አሰራርና የፅንፈኝነት አስተሳሰብን ከራሱ ጀምሮ በቁርጠኝነት መታገል አለበት። 

ፅንፈኝነትና ህገወጥነት አሁናዊ የክልሉ ፈተናዎች መሆናቸውን አስታውሰው፤ የድርጊቱን ፈጻሚዎች ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ መታገልና ስርዓት ማስያዝ ይገባል ብለዋል።

ብልፅግና ፓርቲ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አዲስ አስተሳሰብ የተከለ ፓርቲ መሆኑን አቶ እርዚቅ ጠቁመው፣ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት እንደ አመራር ከእኔ ምን ይጠበቃል ብለን መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

"ፈተናዎች ቢበዙም ወደ ዕድል ቀይሮ ህዝባችንን ተጠቃሚ ለማድረግ በየደረጃው ያለው አመራር ቁርጠኛ ሆኖ በአንድነት መስራት ይኖርበታል" ያሉት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢክስ ወርቄ ናቸው።

አስተዳዳሪው እንዳሉት በኢትዮጵያውያን ማዕቀፍ ውስጥ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር ተባብሮ በመስራት የሀሳብ አንድነትን ማስቀጠልና ችግሮችን መፍታት ያስፈልጋል።

በተመሳሳይ የዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳደሪ ዶክተር ስቡህ ገበያው እንዳሉት፣ ከለውጡ ወዲህ ብልፅግና ፓርቲ አዲስ ራዕይና አስተሳሰብ ይዞ ለህዝብ ተጠቃሚነትን እየሰራ ነው። 

የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በማፋጠን ለአገልግሎት ለማብቃት አመራሩ ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ የሚሆንበት ወቅት መሆኑን ጠቁመዋል። 

የህዝብ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲያገኙ በዴሞክራሲያዊ መልኩ መንቀሳቀስና በአብሮነት መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል። 

የዋግ ህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዳግም ባይነሳኝ እንዳሉት ፓርቲው በፈተናዎች ታጅቦ አገርን ለማስቀጠል እየሰራ ነው። 

"በመሆኑም በየደረጃው ያለን አመራሮች ፅንፈኝነትን በማስወገድ የህዝብን ጥያቄ ለመፍታትና ሰላሙን ለማጠናከር ከወትሮው በተለየ አንድነታችንን ማጠናከር አለብን" ብለዋል። 

በዞኖቹ ዛሬ የተጀመረው ኮንፈረንስ ለሦስት ተከታታይ ቀናት እንደሚካሄድ ታውቋል።

ባለፈው ሳምንት በክልል ደረጃ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የተሳተፉበት ኮንፈረንስ በባህር ዳር ከተማ ለቀናት መካሄዱ የሚታወስ ነው።

 

 

 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም