ባለፉት አስር ወራት ወደ ወጪ ከተላኩ የግብርና ምርቶች 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት አስር ወራት ወደ ወጪ ከተላኩ የግብርና ምርቶች 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ተገኘ

አዲስ አበባ ግንቦት 17/2015 (ኢዜአ) ባለፉት አስር ወራት ወደ ውጪ ከተላኩ የግብርና ምርቶች 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ በዛሬ እለት የተቋማቸውን የ2015 በጀት አመት የአስር ወራት እቅድ አፈጻጸም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል።
ሚኒስትሩ በዕቅድ ሪፖርታቸው ካካተቷቸው ዋና ዋና አፈጻጸሞች ውስጥ የግብርና ምርቶች ወጪ ንግድ አንዱ ነው።
በዚህም የግብርና ሚኒስትር ከሚከታተላቸው የሆርቲካልቸር፣ ቡና፣ ሻይ፣ ቅመማ ቅመምና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች 1 ነጥብ 65 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን ተናግረዋል።
የአለም የቡና ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ ባይመጣ አፈጻጸሙ ከዚህ የተሻለ ገቢ ይገኝ እንደነበር ጠቅሰዋል።
በሌላ ተቋም ክትትል ከሚደረግባቸው የግብርና ምርቶች ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች፣ ጫት፣ የቁም እንስሳትና ሌሎች ዘርፎች ከ687 ሚሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱን አስታውቀዋል።
በዚህም በ2015 በጀት አመት አስር ወራት ወደ ወጪ ከተላኩ የግብርና ምርቶች በአጠቃላይ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር እንደተገኘ ተናግረዋል።
ወደ ውጪ የሚላኩ የግብርና ምርቶች ቁጥጥርን በተመለከተ 835 ሺህ ቶን እጽዋትና የእጽዋት ውጤቶች ጥራታቸውን በማረጋገጥ ለመላክ ታቅዶ 769 ሺህ ቶን መላክ ተችሏል ነው ያሉት።
ለኤክስፖርት የተዘጋጁ 85 ሺህ የቁም እንስሳትን የኤንስፔክሽን እና ሰርተፍኬሽን ስራ ለማከናወን ታቅዶ የ68 ሺህ የቁም እንስሳት ኢንስፔክሽን በማከናወን ወደ ውጭ እንዲላኩ መደረጋቸውን ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡና በአገር ውስጥ የሚመረቱ የግብርና ግብአቶች ላይ ጥራት የማረጋገጥ ስራ መከናወኑን ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ዳሰዋል።