ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነትና ትብብር መጎልበት የምታበረክተውን አስተዋጽዖ አጠናክራ መቀጠል አለባት - ድላሚኒ ዙማ

አዲስ አበባ ግንቦት 17/2015 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጀት ለአሁኑ አፍሪካ ኅብረት ምሥረታ ያበረከተችውን አስተዋጽዖ አሁንም ለአህጉሪቷ ትብብር መጎልበት አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት የቀድሞ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ዶክተር ድላሚኒ ዙማ ገለጹ።

የመጀመሪያዋ ሴት ሊቀ-መንበር በመሆን የአፍሪካ ኅብረትን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2012 አስከ 2017 የመሩት ደቡብ አፍሪካዊቷ ዶክተር ድላሚኒ ዙማ በአፍሪካ ኅብረት 60ኛ ዓመት ክብረ በዓል ለመታደም አዲስ አበባ ገብተዋል።

በክብረ በዓሉ ያለፉት 60 ዓመታት ኅብረቱ ከምሥረታው ጀምሮ እስካሁን የደረሰበትን ደረጃ በማስመልከት ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የአፍሪካ ኅብረት በርካታ ፈተናዎችን አልፎ እዚህ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል።

ከስኬቶቹ መካከል ድርጅቱ በወቅቱ ሲቋቋም ነጻ የአፍሪካን አገራትን ለመፍጠር ያደረገውን ጥረት ለአብነት አንስተው ከዛም በኋላ ፖለቲካዊ ውህደት ያነገበውን ድርጅቱን የተለያዩ ተልዕኮ አንግቦ እንዲንቀሳቀስ ወደ ኅብረት የተሸጋገረበት ጊዜ እንደትልቅ ግብ የሚወሰድ መሆኑን ጠቁመዋል።

"ምንም እንኳን አፍሪካ በርካታ የምንኮራበት ስኬቶች አሉ " ያሉት ዶክተር ድላሚኒ ዙማ፤ አሁንም በርካታ ውስጣዊ የሆኑ ችግሮች ለአህጉሪቱ ፈተና ሆነ መቀጠላቸውን አንስተዋል።

ለአብነትም የእርስ በርስ ግጭት መኖሩና አሁንም የጸጥታ መደፍረስ የአህጉሪቱ ችግር መሆኑን ገልጸው ይህም ሁኔታ እንዲቀየር መሥራት ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም ይህንን ተቋም ይበልጥ በመደገፍና ለቀጣይ ትውልድ አንድነቷ የተጠናከረ፣ የተሳሰረች፣ የበለጸገችና ሰላምና ደኅንነቷ የተረጋገጠ አህጉር ማስተላለፍ እንደሚገባ ገልጸው ለዚህም ኅብረቱና አባል አገራት በጋራ መሥራት አለባቸው ነው ያሉት።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ትግበራ በመልካም ደረጃ ላይ መሆኑን አንስተው በተለይም ኢንዱስትሪን በማስፋት ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።

በአፍሪካ ብልጽግና ለማረጋገጥና በርካታ ሰዎችን ከድኅነት ለማውጣት የውሃ፣ የሃይል፣ የትራንስፖርትና ሌሎች ወሳኝ መሰረተ ልማቶች ሊስፋፉ እንደሚገባ ገልጸው በተለይ አፍሪካ ያላትን ሃብት በመጠቀም ራሷን ልትመግብ ይገባል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት ምሥረታ ከፍተኛ ሚና መጫወቷን የተጠቀሱት ዶክተር ድላሚኒ ዙማ ይህንን ሚናዋን አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት ነው ያሳሰቡት።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊያን መሰባሰቢያ ከተማ ናት፤ ይህንን ደግሞ ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል በማለት ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊያን ያላትን ሚና አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም