ስምንተኛው ሃገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ ነገ በአሶሳ ይጀመራል

203

አሶሳ ግንቦት 17  /2015 (ኢዜአ) ፡-  ስምንተኛው ዓመታዊ ሃገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ   ነገ እንደሚጀመር  የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ። 

ኮንፍረንሱ “የምርምርና ዩኒቨርሲቲ ትስስር ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሄድ  በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አብዱልሙሃሰን ሃሰን ዛሬ ለኢዜአ ገልጸዋል። 

ዓላማው ተመራማሪዎች ምርምራቸውን በማቀናጀት ለሃገር ዘላቂ ልማት የሚያደርጉትን  አስተዋጽኦ ለማጠናከር መሆኑን  አመልክተዋል፡፡

በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የሚካሄደው ኮንፍረንሱ እስከ ግንቦት 19 ቀን  2015 ዓ.ም. እንደሚቆይ  ጠቁመው፤ ከአዲስ አበባ፣ ጎንደር ፣ሃሮማያና ጅማን ጨምሮ የተለያዩ  ዩኒቨርሲቲዎች ይሳተፋሉ ብለዋል፡፡

በዚህ ሀገር  አቀፍ ኮንፍረንስ  25 ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው የሚጠበቅ መሆኑን ዶክተር አብዱልሙሃሰን አስታውቀዋል።

ጥናታዊ ጽሁፎቹ በኢንጂነሪንግና ተክኖሎጂ፣ በተፈጥሮ፣ በጂኦሎጂ፣፣ በግብርና፣ በቢዝነስ፣  በኢኮኖሚክስ፣ በማህበራዊ ሳይንስና ሌሎችም ዘርፎች ላይ እንደሚያተኩሩ ጠቁመዋል፡፡

ሰባተኛው  ሃገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስም በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት መካሄዱንና ይህም  ሳይንሳዊ እውቀቶች በመለዋወጥ ተቀናጅተው መስራት ያስቻለ ግንዛቤ  ተገኝቶበት እንደነበር  አስታውሰዋል፡፡

በስምንተኛው ኮንፍረንስም የሚቀርቡ ጽሁፎች ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርትና የልህቀት ማዕከላትን የመደገፍ ሃገራዊ የትኩረት አቅጣጫን በማገዝ ምርምሮች ወደ ተግባር የሚቀየሩበትን ተሞክሮ የሚያሳድጉ መግባባቶች ይደረስበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም