በሐረሪ ክልል በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከል 2 ሚሊዮን ችግኝ መዘጋጀቱን የግብርና ልማት ቢሮ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከል 2 ሚሊዮን ችግኝ መዘጋጀቱን የግብርና ልማት ቢሮ አስታወቀ

ሐረር ግንቦት 17 /2015(ኢዜአ) ፡- በሐረሪ ክልል በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር የሚተከል 2 ሚሊዮን ችግኝ መዘጋጀቱን የክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ አስታወቀ።
ከዚህ ውስጥ 70 በመቶ የፍራፍሬና 30 በመቶ ደግሞ የደን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን በግብርና ልማት ቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ሙህየዲን መሃመድ ለኢዜአ ገልጸዋል።
እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ ከተዘጋጀው 2 ሚሊዮን ችግኝ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን የፍራፍሬ መሆኑን አመልክተው፤ የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ቁፋሮ ዝግጅትም ከወዲሁ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡
ከፍራፍሬ ችግኙ መካከል ፓፓዬ፣ አቮካዶና ዘይቱና እንደሚገኝበት ጠቅሰው፤ 120 ሺህ የሐረር ቡና ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እስካሁን ባለው ሂደት 85 ሺህ የቡና ችግኝ መሰናዳቱን አስረድተዋል፡፡
በተለይ ዘንድሮ የሚተከለው የፓፓዬ ችግኝ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ፍሬ የሚሰጥ ዝርያ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት የተተከለው የፓፓዬ ችግኝ ለፍሬ ደርሶ በአሁኑ ወቅት ምርቱ ለገበያ እየቀረበ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር በሚከናወነው የችግኝ ተከላ ላይ ህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ከወዲሁ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ መከናወኑን ያመለከቱት አቶ ሙህየዲን፤ በቀጣዩ ሳምንት የፓፓዬ ችግኝ ለማሰራጨት ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
ዝናቡ ከወቅቱ ቀደም ብሎ መጣል መጀመሩ ዘንድሮ የሚተከለው ችግኝ የመፅደቅ መጠንን ከፍ ያደርገዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
ግንቦት 29 ቀን 2015ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አቶ ሙህየዲን አብራርተዋል፡፡
በክልሉ የኤረር ቂሌ ችግኝ ጣቢያ አስተባባሪ አቶ ዘሪሁን አያሌው በበኩላቸው፤ በጣቢያው የደን፣ የተዳቀለ የአቮካዶና የማንጎ ችግኝ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
እስካሁን በጣቢያው 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ችግኝ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።