አፍሪካ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት በመጠቀም ምርታማነቷን መጨመርና ራሷን መመገብ አለባት - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ

አዲስ አበባ  ግንቦት 17/2015  (ኢዜአ) አፍሪካ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት በመጠቀም ምርታማነቷን መጨመርና ራሷን መመገብ መቻል አለባት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።  

የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ አፍሪካ ኅብረት 60ኛ ዓመት ክብረ በዓል በአዲስ አበባ የኅብረቱ ዋና መሥሪያ ቤት በቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንትና የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ በተሠየመው መሠብሠቢያ አዳራሽ ተካሂዷል። 


 

በመርኃ ግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላትና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። 

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤ የ32 የአፍሪካ አገራት መሪዎች የዛሬ 60 ዓመት በአዲስ አበባ ተገኝተው የኅብረቱን መመሥረት የሚያበስረውን ቻርተር መፈረማቸውን አስታውሰዋል። 

አሁን ላይ 55 አባል አገራት  የያዘው አፍሪካ ኅብረት በዓለም መድረክ ጠንካራና ትልቅ ሥፍራ እየያዘ መምጣቱን ጠቁመው በዚህም የአህጉሪቱንና የኅዝቧን ጥቅም ለማስከበር ማስቻሉን ተናግረዋል። 

ያም ሆኖ የአፍሪካ ኅብረት መሥራች አባቶች በኅብረቱ መቋቋሚያ ቻርተር ያሠፈሯቸውን ቃል ኪዳኖችና በአጀንዳ 2063 የተጠቀሱትን ፍላጎቶች ሙሉ በሙሉ በመፈፀም ረገድ ብዙ ይቀራል ነው ያሉት።

አህጉሪቷ አሁንም በድኅነት ውስጥ እየማቀቀች፣ አሰራሮች በሙስና እየተተበተቡ፣ ለገጠሙን ችግሮች አሁንም ከአህጉሪቷ ውጪ ድጋፍ እያፈላለግን ነጻ ነን ማለት አንችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አፍሪካ ያላትን ሃብት በመጠቀም ይህንን ሁኔታ መቀየር አለባት ነው ያሉት። 

በተለይም ደግሞ የአፍሪካ ወጣቶች በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቴክኖሎጂ ዘርፍ በመሳተፍ አህጉሪቷ መቀየር እንደሚገባ ጠቁመው በዚህ ረገድ በተለይም አፍሪካ የመለወጥ አቅም እንዳላት "ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የምትሰራው ውጤታማ ሥራ" ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመዋል።

  በሌላ በኩል አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረክ ተሠሚነቷን ለማጠናከር የሚያስችሉ ዓለም አቀፍ ውክልናዋ መስፋት እንዳለበት ጠቅሰው፤ ለዚህም በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት እንዲሁም በቡድን 20 እና ቡድን ሰባት ተሣትፎ እንዲኖራት መስራት ይገባል ነው ያሉት። 

የአፍሪካ አገራትና ዜጎቿም የአፍሪካ ኅብረት መሥራች አባቶች የያዟቸውን የአንድነት አቋም በማስቀጠል በአፍሪካ አገራት መካከል ጠንካራ ኅብረት ለመመሥረት የሚያደርጉትን ጥረት መቀጠል እንደሚገባ ጠቁመዋል።  

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት፤ አፍሪካ ኅብረት የተለያዩ ተግዳሮቶችን አልፎ አሁንም አህጉሪቱን የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ  እየሰራ ያለ አህጉራዊ ተቋም መሆኑን ጠቁመዋል።    

አፍሪካ ችግሮችን ተቋቁማ የተሻለ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ድምጿም የመሰማት እድል ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል። 

አፍሪካ ላይ ውጪያዊ ጫናዎች መኖራቸው ጠቁመው ይህም አፍሪካን እንዲሁም መላውን ዓለም ትኩረት ያደረጉ የባለብዙ ወገን ሥራዎች ለመሥራት አሉታዊ ጫና እንዳላቸው አንስተዋል። 

በመሆኑም እነዚህና ሌሎች ችግሮችን ለመከላከል አፍሪካ በጋራ መቆም እንደሚገባ ተናግረዋል። 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም