ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በቤጂንግ የተገነባውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መርቀው ከፈቱ

አዲስ አበባ ግንቦት 17/2015 (ኢዜአ)፦ የኢፌዲሪ መንግስት በቻይና ርዕሰ መዲና ቤጂንግ ያስገነባውን አዲስ ኤምባሲና የመኖሪያ ህንጻ በዛሬው እለት አስመርቋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የቻይና የምክር ቤት አባል እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ ኤምባሲውን መርቀው ከፍተዋል፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የኤምባሲው አዲስ ገጽታ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የአጋርነት ጠቀሜታ የበለጠ ለማጠናከር የተወሰደው እርምጃ ተጨባጭ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያና የቻይና የቀደመ ግንኙነት በሁለቱ አገሮች ማካከል ላለው ጥልቅ የሆነ ኢኮኖሚያዊ፣ በባህላዊ እና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር መሠረት የጣለ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ለቻይና-አፍሪካ ትብብር ስኬት ተምሳሌት ለመሆን ተግታ ትሰራለች ብለዋል።

አያይዘውም ኢትዮጵያና ቻይና የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት በሁለትዮሽ በክልላዊና በባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ በጋራ እንደሚቆሙ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡


 

የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ የአዲሱ ኤምባሲ መገንባት የኢትዮጵያ እና የቻይና ግንኙት የበለጠ እንደሚያጠናክር አስታውቀዋል።

የውጭ ገዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው የኤምባሲው ህንጻ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ቻይና ላደረገቸው ያላሰለሰ ትብብር አመስግነው፤ አጅግ በረረቀቀ መልኩ የተገነቡት የኤምባሲው እና የመኖሪያ ቤቱ ህንጻዎች ለትውልድ የሚተርፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በቻይና የኢፌዲሪ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ባደረጉት ንግግር የኤምባሲው ግንባታ የኢትዮጵያና ቻይና ወዳጅነት ሃውልት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም