በህዝብ ተሳትፎ የመጣውን ለውጥ ከዳር ለማድረስ ጽንፈኝነትን በቁርጠኝነት መታገል ይገባል-ዶክተር ድረስ ሳህሉ

108

ባህር ዳር ግንቦት 17/2015  (ኢዜአ)  በህዝብ ተሳትፎ የመጣውን ለውጥ ከዳር ለማድረስ ጽንፈኝነትን በቁርጠኝነት መታገል ይገባል ሲሉ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ገለጹ።

"ፈተናዎችን ወደ ድል በመቀየር ህዝባችን እናሻግራለን" በሚል መሪ ቃል የከተማ አስተዳደሩ አጠቃላይ አመራሮች የተሳተፉበት የሦስት ቀናት ኮንፈረንስ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል። 


 

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በኮንፈረንሱ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፣ ኮንፈረንሱ በየደረጃው ባለው የብልጽግና ፓርቲ አመራርና አባላት ላይ የአስተሳሰብና የአመለካከት አንድነት ለማምጣት ያለመ ነው። 

መድረኩ የፓርቲውን መርሆዎችና እሳቤዎችን በመገንዘብ ራሱን ለመስዋዕትነት የሚያዘጋጅ አመራር ወደ ፊት የሚመጣበት መሆኑንም ጠቁመዋል። 

"በተስተዋሉ ችግሮች ላይ በጥልቀት በመወያየትና በመከራከር ጠቃሚ ሃሳቦችን ለይቶ ከማውጣት ባለፈ ድርጅታዊ ወገንተኝነታችንን የምናረጋግጥበት መድረክ ነው" ያሉት ዶክተር ድረስ፣ አቋምን ለይቶ ለመሰለፍም የሚያስችል ኮንፈረንስ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኮንፈረንሱ የአመራርና የአባላትን አስተሳሰብና አመለካከት ከማጥራት ባለፈ አገራዊ አንድነትን ስለሚያጠናክር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በጥብቅ ዲሲፕሊን ይመራል ብለዋል ዶክተር ድረስ።

በህዝቡ ተሳትፎ የመጣውን አገራዊ ለውጥ በሌላ ድል አጅቦ ለማስቀጠል በሚደረግ ጥረት ጽንፈኛ አካላት እንቅፋት በመፍጠር ህዝቡን ለችግር እየዳረጉ መሆኑንም ዶክተር ድረስ ገልጸዋል።

የለውጥ ጉዞውን ከዳር ለማድረስ አመራሩ አንድነቱን በማጠናከር ጽንፈኝነትን በቁርጠኝነት መታገል እንዳለበትም ተናግረዋል። 

"በቀጣይም መላው የከተማው አመራርና አባላት ችግሮችን ተረባርቦ በመፍታት የተቀመጠውን የብልጽግና ግብ ማሳካት አለብን" ሲሉም አስገንዝበዋል።

ለእዚህም የሀሳብና የአፈጻጸም ልዩነትን ወደ አንድ በማምጣት የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ማፋጠን ይገባናል ብለዋል።

ዶክተር ድረስ እንዳሉት ኮንፈረንሱ ባለፉት አምስት ዓመታት በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊና ፖለቲካዊ ልማቶች የመጡ ለውጦችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለማረም ፋይዳው የጎላ ነው።  

ህዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎችን ለይቶ ለመፍትሄው የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ መድረኩ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። 

ለዚህም መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄዎችን መለየት፣ የመፍትሄ ስልቶችን መቀየስና ለተግባራዊነቱ የጋራ አቋም ወስዶ መንቀሳቀስ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

የቱሪስት መስህብ የሆነችውን የባህር ዳር ከተማና የነዋሪዎቿን ሰላም አጠናክሮ ማስቀጠል የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ሃላፊነት መሆኑንም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አመልክተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም