በኢትዮጵያ ከ12 ሚሊየን በላይ እማወራና አባወራዎች በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ስርዓት ተጠቃሚ ሆነዋል- የጤና መድን አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ከ12 ሚሊየን በላይ እማወራና አባወራዎች በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ስርዓት ተጠቃሚ ሆነዋል- የጤና መድን አገልግሎት
አዲስ አበባ ግንቦት 17/2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ከ12 ሚሊየን በላይ እማወራና አባወራዎች በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ስርዓት ተጠቃሚ ማድረጉን የኢትዮጵያ ጤና መድን አገልግሎት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ጤና መድን አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉቀን አርጋው፤ ከ11 ዓመት በፊት የተጀመረው የጤና መድን አገልግሎት ማህበራዊና ማህበረሰብ አቀፍ በሚል ሁለት አይነት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ማሕበራዊ ጤና መድን መደበኛ ወርሃዊ ገቢ ያላቸውን አባላት ሲያካትት ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ደግሞ በኢመደበኛ ስራዎች የተሰማሩና ወርሃዊ መደበኛ ገቢ የሌለውን አብዛኛው የገጠር ህብረተሰብ የሚያጠቃልል መሆኑን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ በተለይም በገጠር በመኖሩ ዜጎች የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አገልግሎት ቀዳሚ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ጠቅሰው በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይና ደቡብ ክልሎች በተመረጡ 13 ወረዳዎች ቀደም ብሎ መጀመሩን አስታውሰዋል።
አሁናዊ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ሽፋን ከመላ ሀገሪቷ ወረዳዎች 89 በመቶውን በመሸፈን በ987 ወረዳዎች ተደራሽ በማድረግ 12 ነጥብ 3 ሚሊዮን እማወራና አባወራዎች ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።
በቤተሰብ ደረጃ በአማካይ ከ56 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገ ስራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በአርብቶ አደር አካባቢዎች ያለው ሽፋን ውስን በመሆኑ አገልግሎቱ በተዘረጋባቸው ወረዳዎች ተደራሽ ያልሆኑ እንዳሉ ጠቁመዋል።
የጤና መድን ለዜጎች የህከምና አገልግሎት ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ እንደ ሀገር ጤናማ ማህብረሰብ ለመፍጠር እገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በየደረጃው የአመራር ቁርጠኝነት ማነስ፣ የአቅርቦት ጥራት ጉድለት፣ የፋይናንስ ችግርና የሰራተኛ ፍልሰት ለውጤታማ ጤና መድን ሽፋን ተደራሽነት ላይ ተግዳሮቶች መሆናቸውንም ዶክተር ሙሉቀን አንስተዋል።
በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አዋጅ ማውጣትን ጨምሮ የአሰራር ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።