የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ለፕራይም ቴሌቭዥን የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ለፕራይም ቴሌቭዥን የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጠ
አዲስ አበባ ግንቦት 17/2015(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ለፕራይም ቴሌቭዥን የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 መገናኛ ብዙኃን በዜጎች መካከል አብሮነትን ከሚሸረሽር እና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለአለመተማመን ከሚዳርግ የይዘት ስርጭት እንዲቆጠቡ ግዴታ እንደሚጥል ገልጿል።
በኢፌዴሪ ህገመንግስት ፣በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ እና ሌሎች ተያያዥ ህጎችም የመገናኛ ብዙሃን በተለይም የጋራ እሴቶችን የሚንዱ አለመቻቻል እንዲፈጠር ምክንያት የሚሆኑ እና ዜጎችን ለግጭት ሊያነሳሱ የሚችሉ ስርጭቶችን ከማስተላለፍ እንዲታቀቡ ይደነግጋሉ።
ፕራይም ቴሌቭዥን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እነዚህን ህግጋት የሚጥሱ ዜናዎችንና ፕሮግራሞችን ሲያሰራጭ መቆየቱን በክትትል ስራችን አረጋግጠናል ያለው ባለስልጣኑ በዚህም በተደጋጋሚ እርምት እንዲወስድ ግብረ-መልስ መሰጠቱንና ውይይትም መደረጉን ገልጿል።
ይሁን እንጂ ስህተቱን በመቀጠሉና የዜጎችን አብሮነት የሚጎዳ ይልቁንም ከፍተኛ ጥንቃቄ በሚሹ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ዙሪያ አሉታዊና ህግን የሚተላለፉ ይዘቶችን በማሰራጨት ዜጎችን ላልተገባ ውጥረትና አደጋ ለማጋለጥ አስተዋጽኦ የማድረግ አዝማሚያ እንደታየበትም ባለስልጣኑ አስታውቋል።
በመሆኑም ፕራይም ቴሌቭዥን እንደ ንግድ ብሮድካስተር ከገባው የውል ግዴታና ከተቋቋመለት ዓላማ አንጻር ያልተገባ ተግባር እንደሆነ በመግለጽ ከድርጊቱ እንዲታረም የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አስታውቋል።