የአየር ንብረት ለውጥ በግብርና ልማት ላይ የሚያደርሰውን ተጽእኖ ለመከላከል የምርምር ማዕከላትን ጥምረት በማጠናከር በትብብር መስራት ይገባል- ዓለም አቀፉ እንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት

261

አዲስ አበባ ግንቦት 17/2015(ኢዜአ)፡- የአየር ንብረት ለውጥ በግብርና ልማት ላይ  የሚያደርሰውን ተጽእኖ ለመከላከል ዓለም አቀፍ የምርምር ማዕከላትን ጥምረት በማጠናከር በትብብር መስራት እንደሚገባ ዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ በአነስተኛ እርሻ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን አቅም ለማጎልበት የሚደረገውን የግብርና መዋቅራዊ ለውጥ በተመለከተ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የተሳተፉበት አውድ ጥናት ተካሂዷል፡፡

የዓለም አቀፉ እንስሳት ምርምር ማዕከል በኢትዮጵያ ተወካይ ዳይሬክተር ዶክተር ናሙኮሎ ኮቪች፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጣናው ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለከፋ ድርቅና የጎርፍ አደጋ እየተጋለጡ ነው ብለዋል።

በዚህም በዝቅተኛ እርሻ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች በምርምር የታገዘ ድጋፍና ክትትል ካልተደረገላቸው ችግሩን መቋቋም ይሳናቸዋል ብለዋል፡፡

በመሆኑም መንግስታት፣ የዘርፉ ተዋንያንና ተመራማሪዎች እንደ ዓለም አቀፉ የግብርና ምርምር ማዕከላት ጥምረት ያሉ ተቋማትን አቅም ማጎልበት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡

በአነስተኛ እርሻ የሚተዳደሩ አርሶ አደሮች ላይ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ተጽእኖ ለመከላከል ዓለም አቀፍ የግብርና ምርምር ማዕከላትን ጥምረት በማጠናከር በትብብር መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ፤ በኢትዮጵያ 11 የሚደርሱና በተለያዩ ዘርፍ የተሰማሩ የዓለም አቀፍ የግብርና ምርምር ማዕከላት ጥምረት ተቋማት እንዳሉ ገልጸዋል፡፡


 

እነዚህ ተቋማት በግብርና፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በምግብ ዋስትና መሰል ጉዳዮች ላይ የተሟላ ጥናትና ምርምር በማካሄድ መረጃና ምክረ ሀሳብ የሚያቀርቡ ናቸው ብለዋል፡፡

የምርምር ተቋማቱ በኢትዮጵያ እንዲሁም በቀጣና እና ዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ ጥናትና ምርምር በማድረግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፤ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘትና የስራ ዕድል ለመፍጠር እገዛ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዓለም ባንክ ግሩፕ የግብርናና ምግብ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ዳይሬክተር ዶክተር ማርቲ ቫን ኒውኮፕ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል የሚያስችሉ አስደናቂ ውጤቶችን ማስመዝገቧን ገልጸዋል፡፡


 

የዓለም አቀፍ ግጭቶች፣ የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋት የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እንቅፋት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ መሰል ችግሮች ሲያጋጥሙ ሀገራት በትብብር መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የዓለም ባንክ በዝቅተኛ እርሻ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርስባቸውን ተጽዕኖ ለመቀነስ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ አረጋግጠዋል።

የግብርና ሚኒቴርና የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ከዓለም አቀፍ የግብርና ምርምር ማዕከላት ጥምረት ጋር በመተባበር አውደ ጥናቱ መዘጋጀቱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም