የምርምር ማዕከሉ ለአካባቢው ስነ-ምህዳር ምቹና ውጤታማ የሆኑ የግብርና ምርቶች እያስተዋወቀ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የምርምር ማዕከሉ ለአካባቢው ስነ-ምህዳር ምቹና ውጤታማ የሆኑ የግብርና ምርቶች እያስተዋወቀ መሆኑን ገለጸ
ጭሮ፤ግንቦት 17/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጭሮ ማሽላ ምርምርና ማሰልጠኛ ማዕከል ለአካባቢው ስነ-ምህዳር ምቹና ውጤታማ የሆኑ የግብርና ምርቶች እያስተዋወቀ መሆኑን ገለጸ።
የምርምር ማዕከሉ ዳይሬክተርና ተመራማሪ አቶ አብዱልፈታ ታሪኩ ለኢዜአ እንደገለጹት ማዕከሉ ከአካባቢው የአየር ፀባይና መልከዓምድራዊ አቀማመጥ ጋር ተስማሚ የሆኑ የግብርና ምርቶችን እያስተዋወቅ ነው።
ማዕከሉ በሚገኝበት ምዕራብ ሀረርጌ ዞን በምርምር የወጡ የምርጥ ዘር ዝርያዎችንና ስልጠናዎችን ለአርሶ አደሩ እየሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ማሽላ፤ ማሾና ሌሎችንም ከአካባቢው ጋር ማለማድ እንደተቻለ ገልጸው በተለይ በዞኑ ቆላማ የሆኑ ሚኤሶና ቦርደዴ ወረዳዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ማሾን አምርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
ለዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤትም መነሻ የምርጥ ዘር በመስጠት የማስፋፋትና አርሶ አደሩ በዓመት አንዴ ከማምረት ተላቆ በአመት 2 እና 3 ጊዜ ምርት መሰብስብ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
ከማሽላና ማሾ ሌላ ጤፍ፣ ቦሎቄ፣ ሽምብራ፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ቃሪያና ስምንት አይነት የወይን ዝርያዎች በማዕከሉ አማካኝነት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ ከአካባቢው አየር ጋር የሚስማሙና በመስኖ የሚለሙ የተለያዩ የስንዴ ምርጥ ዘር ለአካባቢው አርሶ አደር ይሰራጫልም ብለዋል።
የማዕከሉ የሰብል ምርምር ተመራማሪ አቶ ስንታየሁ ሀይሉ ማዕከሉ የዞኑ አርሶ አደሮች የማሽላ ምርጥ ዘር ዝርያዎች በማልማት በምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡና ለገቢያም እንዲያቀርቡ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የዞኑ አርሶ አደር በአመት አንዴ ከማምረት ተላቆ በ3 እና 4 ወራት የሚደርሱ በብዛትም በጥራትም ማምረት እንዲችል እገዛ እየተደረገለት መሆኑን አስታውሰዋል።
የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሁሴን መሀመድ በበኩላቸው ከምርምር ማዕከሉ ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የዞኑ አርሶ አደሮች በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጡ እና ድርቅ መቋቋም የሚችሉ የተለያዩ የማሽላ ዝርያዎችን ከማዕከሉ እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡
ከነዚህም መካከል ማሾ፣ ማሽላ፣ ቦሎቄ፣ ሽምብራና ሌሎች በምርምር የወጡ አዳዲስ የግብርና ምርቶችን እየተጠቀሙ መሆኑን አስረድተዋል።
በዞኑ በጋ መስኖ ልማት ከ20 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት ላይ የማሽላ ምርጥ ዘር መዘራቱን ገልጸው በዚህም ከ800 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሩ ቀደም ባለው ጊዜ በሔክታር ከ10 እስከ 15 ኩንታል ያገኝ እንደነበር ጠቅሰው ምርጥ ዘር መጠቀም ከጀመረ ወዲህ ከ35 እስከ 40 ኩንታል ምርት እያገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዞኑ አርሶ አደሮች መካከል መካከል አባድር ሱሌ ምርጥ ዘር ለመውሰድ በማእከሉ መገኘታቸውን ጠቁመው ባለፈው አመት የማሽላ ምርጥ ዘር ከምርምር ማዕከሉ ወስደው በመዝራት በ3 ወራት የተሻለ ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
''የማዕከሉ ተመራማሪዎች በእርሻ ቦታዎች ላይ እየተዘዋወሩ ምርጥ ዘርን ከማዳበሪያ ጋር እንዴት መጠቀም እንዳለብን በተግባር ስልጠና በመስጠት እየደገፉን ይገኛሉ'' ብለዋል፡፡
አርሶ አደር መሀመድ ቶፊቅም ከማዕከሉ የተለያዩ የማሽላ ምርጥ ዘሮችን በመውሰድ እያመረተ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡
''በፊት በዘጠኝ ወር የሚደርስ ማሽላ ዘርቼ የማገኘው ትርፍ ብዙም አልነበረም'' በተሻሻለው ምርጥ ዘር ግን ከ30 ኩንታል በማምረት ለገበያ ጭምር ማቅረብ መቻሉን አስረድቷል።