በኦሮሚያ ክልል ለዘንድሮው ዓመት አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ4 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ተዘጋጅቷል - የክልሉ ግብርና ቢሮ

269

አዲስ አበባ ግንቦት 17/2015 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ለዘንድሮው ዓመት አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ4 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መዘጋጀቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ  ኤሊያስ ከድር፤ በ4ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የኦሮሚያ ክልል ከ4 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ነው የተናገሩት፡፡

በአጠቃላይ በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞች የአካባቢን ሚዛን በመጠበቅ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራን በማሻሻል ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆኑንም  ገልጸዋል፡፡

ለዘንድሮው ዓመት አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብርም በክልሉ 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው፤ በዋናነት ለፍራፍሬ ችግኞች ትኩረት በመስጠት የችግኝ ማፍላት ስራ ሲከናወን መቆየቱን ተናግረዋል። 

ለችግኝ ተከላ የሚሆን ቦታ መረጣና ጉድጓድ ዝግጅትም ቀደም ብሎ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በክልሉ 13 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ጠቅሰው፤ የጽድቀት መጠናቸውንም 88 ነጥብ 6 በመቶ ማድረስ እንደተቻለ ተናግረዋል። 

ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በበጋው ወቅት 6 ሺህ 450 ተፋሰስ ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መከናወኑንም ጨምረው ገልጸዋል። 

በተጨማሪም ከ500 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የተራቆተ አከባቢ ከንክኪ ነጻ ማድረግ መቻሉንም ነው የተናገሩት፡፡

በክልል ደረጃ ከሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብሩ እንደሚካሄድ ጠቁመው፤ ለዚህም በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን በበጎ ፈቃድ ለማሳተፍ  ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በዘንድሮው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአገር ዓቀፍ ደረጃ 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ዝግጅት በመካሄድ ላይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ማሳወቃቸው ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም