በውኃ ሀብት አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ የሚታዮ ችግሮችን ለመፍታት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በውኃ ሀብት አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ የሚታዮ ችግሮችን ለመፍታት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
ሻሻመኔ ግንቦት 17/2015 (ኢዜአ):- በውኃ ሀብት አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ የሚታዮ ችግሮችን ለመፍታት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተፋሰስ ዕቅድ፣ የህግ ማዕቀፎች፣ የውኃ ሀብት አጠቃቀምና ተግዳሮቶች እንዲሁም የውሃ ሀብት መረጃዎች ዙሪያ ከሲዳማና ደቡብ ክልል ለተውጣጡ የዘርፉ አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጥቷል።
በዚሁ ወቅት የውኃና ኢነርጅ ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ደበበ ደፈርሶ እንደተናገሩት በውሃ ሀብት አጠቃቀምና አስተዳደር ዙሪያ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት እየተሰራ ነው።
በተለይም ግብርናውን የበለጠ ለማዘመንና አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የውሃ ሃብት አጠቃቀምና አስተዳደርን ማሻሻል አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ይህም በመሆኑ በውሃ ሀብት አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ የሚታዩ የቅንጅት፣ የመረጃ አያያዝና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በውኃ ሃብት አጠቃቀም እና አስተዳደር ዙሪያ በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሲዳማና በደቡብ ክልሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱን አስታውሰው ይህው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በተያያዘም ከክረምት ጋር ተያይዞ የአዋሽ እና ኦሞ ወንዞች ሞልተው ዜጎች ላይ ጉዳትና መፈናቀል እንዳይደርስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰፊ ስራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በሚኒስቴሩ የተቀናጀ ውኃ አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ በላይነህ ይርዳው በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ሰፊ የውኃ ሃብት ቢኖራትም ባለው የውኃ ሀብት አስተዳደርና የመረጃ ክፍተት ምክንያት የውኃ ሃብቱ በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ይላሉ።
በኢትዮጵያ ዓመቱን ሙሉ ከሚፈሱ ከ12 ተፋሰሶች ብቻ በዓመት 122 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የገጸ ምድር ውሃ ቢኖራትም አብዛኛው የውኃ ሀብት በስራ ላይ ሳይውል እየባከነ መሆኑን አስረድተዋል።
ችግሩን ለመፍታት በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማብዛት እንዲሁም ተመራማሪዎችና ፖሊሲ አውጪዎች ተቀናጅተው እንዲሰሩ ይደረጋል ነው ያሉት።
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የውሃና ኢነርጅ ቢሮ ኃላፊ አቶ አክሊሉ አዳኝ፤ በክልሉ የውኃ ሀብት አስተዳደርና አጠቃቀምን ለማሻሻል ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬ የተሰጠው በዘርፉ ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ስልጠናም የተጀመሩ ስራዎችን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚረዳም አስገንዝበዋል።