ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረገው ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል-ፌዴሬሽን ምክር ቤት

አዲስ አበባ ግንቦት 17/2015(ኢዜአ)፡-  በኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ ሀገራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረገው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

አፈጉባዔ አገኘሁ ይህን ያሉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና ከኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጋር በትብብር መስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት በተፈራረመበት ወቅት ነው።


 

በስነስርዓቱ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ትነበብ ብርሃኔ ተገኝተዋል፡፡

አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የስምምነቱ ዋና ዓላማ ሀገራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዩች ላይ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ ማስቻል ነው፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሀገሪቱ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጎልበትና ፍትሓዊ የሀብት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘላቂ ሰላም፣ አንድነትና ኢኮኖሚያዊ እድገትን በማሳካት የፌዴሬሽኑን ተልዕኮ እንደሚያግዙ አንስተዋል።

መንግስት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሲቪል ማህብረሰብ ድርጅቶች በመላው ሀገሪቱ ተንቀሳቅሰው ስራቸውን ያለምንም እንቅፋት እንዲያከናውኑ ከአዋጅ ማሻሻያ ጀምሮ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸውም ተናግረዋል።፡

ዛሬ የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነትም ድርጅቶቹ ሚናቸውን ይበልጥ በማስፋት ለሀገር እድገትና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን እንዲወጡ ያስችላል ነው ያሉት አፈ ጉባዔው፡፡

የህግ ተገዥነት፣ ህገ-መንግስታዊነት፣ ግጭት አፈታትና የሰላም ግንባታ የትብብሩ መስኮች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለስምምነቱ ተግባራዊነት የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም በመጥቀስ፤ የኢትዮጵያን ህብረ ብሔራዊ አንድነት ለማጠናከር ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረገው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ የሲቪል ድርጅቶች ለሀገረ መንግስት ግንባታው የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ያስችላል ብለዋል፡፡ 

ስምምነቱ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እንደሚያጠናክር የተናገሩት የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ትነበብ ብርሃኔ ናቸው፡፡ 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም