በምስራቅ ሸዋ ዞን የቆላ የፍራፍሬ ዛፎች ለመትከል ዝግጅት ተጠናቋል - የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት

123

አዳማ ግንቦት 17/2015 (ኢዜአ)  በመጪው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለደን አገልግሎት ከሚውሉ ችግኞች በተጨማሪ በቆላማ የዞኑ አካባቢዎች የፍራፍሬ ዛፎች ለመትከል ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን የምስራቅ ሸዋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ መስፍን ተሾመ እንደገለጹት በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዞኑ ከ200 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ከዚሁ ጋር በዞኑ ቆላማ አካባቢዎች ፍራፍሬ ዛፎች ለመትከል የችግኝ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት በ11 የዞኑ ወረዳዎች የጉድጓድ ዝግጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የቴምር፣ ዘይቱና፣ ግሽጣ፣ አቮካዶ እንዲሁም የቀርካሃ  ችግኞች መዘጋጀታቸውን የገለጹት ሃላፊው ከመጪው ወር ጀምሮ ወደ ተከላ ለመግባት የቅድመ ዝግጅት ስራ እያከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል።

ለእቅዱ ስኬታማነትም በ52 የችግኝ ጣቢያዎች ዘርፈ ብዙ አገልግሎትና ጥቅም የሚሰጡ ችግኞች መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።

አምና በዞኑ ከተተከሉት ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ መፅደቃቸውን ጠቅሰው ከዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ፕሮግራም ጎን ለጎን ለተተከሉት ሰፊ የእንክብካቤ ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

 የተራቆቱ መሬቶችን ከሰውና እንስሳት ንክኪ ነፃ በማድረግ ረገድ በዘንድሮ ዓመት 500ሺህ ሄክታር ለማካለል እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ይህም ለስራ አጥ ወጣቶች  አማራጭ የስራ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት 38 ሺህ ለሚሆኑት ዜጎች በችግኝ ዝግጅት እንዲሁም ከደንና ከደን ውጤቶች ጋር በተያያዘ የስራ እድል መፈጠሩን ጠቅሰው ዘንድሮ ደግሞ 60ሺህ ለሚሆኑት ዜጎች በዚህ ዘርፍ የስራ እድል ለመፍጠር አቅደው እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በእስከ አሁኑ ሂደት ከ45ሺህ በላይ ለሚሆኑት ወጣቶችና ሴቶች የስራ እድል በዘርፉ መፈጠሩን ሃላፊው አክለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም