ፕሬዝዳንት ፑቲን ለአፍሪካ ህብረት 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የእንኩዋን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

1300

አዲስ አበባ ግንቦት 17/2015 (ኢዜአ)፦የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን ለቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ለአሁኑ የአፍሪካ ህብረት 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የእንከዋን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ፕሬዝዳንቱ ባስተላለፉት የእንኩዋን አደረሳችሁ መልዕክት የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት ለአፍሪካውያን የድል ምልክት ነው ያሉ ሲሆን የአፍሪካውያን የነጻነት፣የሰላምና የብልጽግና ፍላጎት ማሳያ ነው ብለዋል።

ህብረቱ ከተመሰረተበት ግዜ አንስቶ ለብዙ አስርተ ዓመታት በዓለም አቀፍ መድረኮች አፍሪካውያንን በመወከል የባለብዙ ወገን ውይይቶችንና ትብብርን በማጎልበት ትልቅ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።

የአፍሪካ ሀገራት ለችግሮቻቸው በጋራ ምላሽ የሚሰጡበትን መንግድ ያመቻቸ መሆኑን ጠቁመው አህጉራዊ ትብብርን በተለያዩ መስኮች እንዲያጠናከሩም መንገድ ከፍቷል ብለዋል።

በዚህም ለአፍሪካ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የላቀ ሚና ማበርከቱንና አፍሪካ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ያላትን ተሳትፎ እንድታሳድግ ህብረቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

በመሆኑም ሩሲያ ከአፍሪካ አጋሮቿ ጋር ያላትን ወዳጅነት ለማጠናከር ልዩ ትኩረት ትሰጣለች ያሉት ፕሬዝዳንቱ እ.አ.አ በ2019 የተካሄደው የመጀመሪያው የአፍሪካ -ሩሲያ ጉባኤ በአፍሪካና በሩሲያ መካከል ያሉ ትብብሮች እንዲጠናከሩ አስችሏል ብለዋል።

በመጪው ሃምሌ ወር በሩሲያ የሚካሄደው ሁለተኛ የአፍሪካ ሩሲያ ጉባኤም ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር ለሚኖራት ትብብር አዲስ ምዕራፍ እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም