ቀጥታ፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋን ጋር ተወያዩ


አዲስ አበባ ግንቦት 17/2015(ኢዜአ)፦ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት በቻይና የሚገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋን  ጋር ተወያዩ።

በውይይታቸው በኢትዮጵያና ቻይና ህዝቦችና መንግስታት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ሁለንተናዊና ስትራቴጂካዊ የትብብር አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡
በተለያዩ የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ተባብረው ለመስራትም ከመግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡


 

አቶ ደመቀ በተባበሩት መንግስታት እና በተለያዩ የአለም ዓቀፍ መድረኮች ላይ ከቻይና ጋር በጋራ ለመስራት ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡

ቻይና የኢትዮጵያ ዋነኛ የኢንቨስትመንት ምንጭ፣ ትልቋ የንግድ አጋር እና የልማት ፋይናንስ አመንጭ መሆኗን በመጠቆም ኢትዮጵያ ባሳየችው ፈጣን የእድገት ጉዞ ቻይና ላደረገችው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋን በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ ሚና የምትጫወት ስትራቴጂካዊ አጋር እንደመሆኗ በቻይና-አፍሪካ ትብብር (ፎካክ) እና ቤልት ኤንድ ሮድ ማዕቀፍ (ቢ አር አይ ) በጋራ በመስራት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማሳደግ ቻይና እንደምትፈልግ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ የቻይና ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው መዋዕለንዋያቸውን እንዲያፈሱ መንግስታቸው እንደሚያበረታታ ተናግረዋል፡፡

ቺን ጋን አክለውም የኢትዮጵያ መንግስት የጀመረውን የመልሶ ማቋቋም እና ዳግም ግንባታ ስራ ቻይና እንደምትደግፍ ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ እና ቻይና መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት ተደራሽነት ለማስፋት እና የጋራ ተጠቃሚነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ የኢትዮጵያ ቻይና (ጓንዶንግ) ፎረም ግንቦት 20 ቀን 2015 ዓ.ም በጓንዶንግ ክፍለ ሃገር ጓንዦ ከተማ የሚካሄድ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም