የአማርኛ ቋንቋን በሞስኮ ትምህርት ቤቶች ማስተማር ሊጀመር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአማርኛ ቋንቋን በሞስኮ ትምህርት ቤቶች ማስተማር ሊጀመር ነው
አዲስ አበባ ግንቦት 17/2015 (ኢዜአ):- በሞስኮ ትምህርት ቤቶች እ.ኤ.አ ከመስከረም 2023 ጀምሮ አማርኛ ቋንቋን ማስተማር ሊጀመር መሆኑ ተጠቆመ።
የሩሲያው የዜና አገልግሎት እና ሬዲዮ ስርጭት አገልግሎት ስፑትኒክ ኢንተርናሽናል በሩሲያ - አፍሪካ የኢኮኖሚ ትብብር ላይ ያተኮረ ውይይት አካሄዷል።
ውይይቱ የተካሄደው በአሌክሳንደር ጎርቻኮቭ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ፈንድና የሰብአዊ እርዳታ ማዕከል ትብበርና ድጋፍ አማካኝነት መሆኑ ተገልጿል።
በውይይቱ ላይ ከሩሲያ እና አፍሪካ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ የታሪክ ተመራማሪ ምሁራንና የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የእስያና አፍሪካ ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አሌክሲ ማስሎቭ አራት የሞስኮ ትምህርት ቤቶች ለህጻናት የአማርኛ እና የስዋሂሊ ቋንቋን እ.ኤ.አ መስከረም ከ2023 ጀምሮ ማስተማር እንደሚጀምሩ ጠቁመዋል።
በአዲሱ ልዩ መርሐ-ግብር በሞስኮ ትምህርት ቤቶች የናይጄሪያውን ዮሩባ ቋንቋን የሚያስተምሩበትን ሁኔታ እየተመቻቸ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
የአፍሪካ የኢኮኖሚ እድገት የተረዱ ባለሙያዎችን ማፍራት ያስፈልጋል ያሉት ዳይሬክተሩ “አፍሪካ ከአህጉርነት ባለፈ የተለያዩ ባህል፣ቋንቋ፣ሃይማኖት እና ህብረ ብሔራዊ ማንነቶች ያሉባት መሆኗን መረዳት ያስፈልጋል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች አፍሪካ እና ሩሲያ በትምህርት ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ማጎልበት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
ግብርናና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ላይ አገራቱ ያላቸውን ትብብር ማጠናከርና ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
ውይይቱ በሩሲያ፣ በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ አገራት መካከል አዲስ ትብብር ለመፍጠር ያለመ የባለሙያዎች እና ትምህርታዊ ዝግጅት አካል መሆኑን ከሩሲያው የዜና አገልግሎት እና ሬዲዮ ስርጭት አገልግሎት ስፑትኒክ ኢንተርናሽናል የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የሩሲያው ስፑትኒክ ኢንተርናሽናል በመስከረም ወር 2012 በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው