ቀጥታ፡

የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ አፍሪካ ኅብረት 60ኛ ዓመት በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 17/2015 (ኢዜአ)፡-የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ አፍሪካ ኅብረት 60ኛ ዓመት በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ነው።

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከኬንያው ፕሬዝዳንት ጆሞ ኬንያታ፣ ከጋናው ፕሬዝዳንት ኩዋሜ ንኩሩማህ፣ ከግብጹ ፕሬዝዳንት ጋማል አብዱል ናስር፣ ከታንዛኒያው ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ኔሬሬ፣ ከጊኒው ሴኮ ቱሬና ሌሎችም መሪዎች ጋር በመተባበር ነበር የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ አፍሪካ ኅብረት የተመሰረተው የዛሬ 60 ዓመት እ.ኤ.አ ግንቦት 25 ቀን 1963 ነው። 

በአህጉሪቱ በአፍሪካ አገራት መካከል ትብብርን ለመፍጠር፣ የትኛውንም አይነት የቅኝ አገዛዝ ሥርዓት ለማስወገድ እንዲሁም የአገራትን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስከበርና ሌሎች ግቦችን በመሰነቅ ነበር በ32 አገራት በአዲስ አበባ የአፍሪካ የመጀመሪያ የድኅረ ቅኝ ግዛት አህጉራዊ ተቋም በመሆን የተመሰረተው።   

ለኅብረቱ መመሥረት ትልቅ ሚና የነበራት ኢትዮጵያ በተለይም የካዛብላንካና የሞኖሮቪያ ቡድኖች የአፍሪካ አንድነት ምሥረታ በተመለከተ የነበራቸው ልዩነት በወይይት በማጥበብና  ወደ አንድ መሥመር በማምጣት በኋላም የአፍሪካ አገራት አንድነትን የሚያጠናክር ድርጅት እንዲፈጠር ከፍተኛውን ሚና መጫወቷን የታሪክ ድርሳናት ያሳየሉ። 

ኢትዮጵያ ሁለቱን ቡድኖች በማስታረቅና የወቅቱን ነባራዊውና መጪውን ጊዜ ያማከለ እንቅስቃሴ  እንዲሁም በአጠቃላይ አፍሪካንና ሕዝቧቿን ጥቅም በሚያስከብር መልኩ በሰራችው ሥራ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቀመጫ አዲስ አበባ እንዲሆን አስተዋጽዖ አድርጎላታል። 

ኢትዮጵያም ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ከሰጠችው ትኩረት ጎን ለጎን ለፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ማበብ እንዲሁም ለአህጉራዊ አንድነት ትኩረት ሰጥታ ተንቀሳቅሳለች። 

ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት ብቻ ሳይሆን አህጉሪቱ ከቅኝ ግዛት ቀንበር እንድትላቀቅ የነጻነት ትግሉን በመደግፍ አዎንታዊ አብርክቶ የነበራት ሲሆን ለአብነትም ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ሥርዓት እንድትላቀቅ በኋላ ላይም ለዙምቧቤ የነጻነት ትግል ስኬት ያደረገችው አስተዋጽኦ ተጠቃሽ ነው።     

አገራት በውስጣቸው የነበሩ አለመግባባቶች እንዲፈቱ እንዲሁም የእርስ በርስ ግጭት ወደ ኋላ በመተው አንድነታቸውን በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ እንዲያጠናክሩ ወደ አህጉራዊ አጀንዳ እንዲያመዝኑ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግም ትታወቃለች። 

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ የነበራትን ሚና በማጠናከር ለአፍሪካ ጉዳይ ያላትን ቁርጠኝነት ሳታወላውል በተለያዩ መንግሥታዊ ሥርዓት ውስጥ በማስቀጠል አሁንም ለአፍሪካ ያላትን ወገንተትነት በተግባር እያሳያች ያለች አገር ናት። 

ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥረታ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ጀምሮ ኢትዮጵያ በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሰላኝ እንዲሁም አሁን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መሪነት ኢትዮጵያ አፍሪካዊ ሚናዋን ቀጥላለች።   

ይህም በአየር ንብረት ለውጥ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ወግና የተከራከረችበትን እንዲሁም አህጉሪቱን በጽኑ በሚፈትናት በሰላምና ደኅንነት ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ ጎረቤት አገራትን ጨምሮ ለሌሎች አፍሪካ አገራት ወታደር እስከ ማቆም የደረሰ ቁርጠኝነቷን አሳይታለች። 

ከአፍሪካ አገራትና ሕዝቦች ጋር በጋራ የመልማት መርህን በመከትልም በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጨምሮ ሌሎችንም ተግባራዊ እንቅስቃሴ የጀመረች ሲሆን በመላው አፍሪካ ይህንን አስተሳሰብ እንዲሰርጽ በባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ጭምር መሞገቷን ቀጥላበታለች። 

በተለይም ኅብረቱ እ.ኤ.አ በ2013 በሃምሳ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ማለትም በ2063 አጀንዳ በፖለቲካ፣ በምጣኔ ኃብት እንዲሁም በማኅበራዊ መስኩ የተሻለ አፍሪካ ለመመሥረት የሰነቀው ግብ እንዲመታ ኢትዮጵያ የበኩሏን አስተዋጽዖ ለማድረግ እየሰራች ትገኛለች። 

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት ከነበሩት ዋና ዋና ፍላጎቶች በተለይም ፖለቲካዊ አንድነት ከመፍጠር አንጻር ግቡን መቷል ቢባልም አፍሪካ ኅብረት ሌሎች ግቦቹን በማሳካት ብዙ የሚቀረውና አሁንም በርካታ ፈተናዎች እየተጋፈጠ የሚገኝ አህጉራዊ ተቋም ነው። 

በአፍሪካ በተለይም ድኅነትን በማጥፋት፣ የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ፣ ሰላምና ደኅንነት ማስፈን እንዲሁም ሌሎች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በመገንባት ረገድ አፍሪካ ኅብረት አሁንም አገራትን በማስተባበር ብዙ ርቀት መጓዝ ያለበት ድርጅት ነው።    

የተሻለች አህጉር ለመፍጠር በሚደረገው አህጉራዊ ጥረት ኢትዮጵያ የራሷን አስተዋጽዖ በማድረግ ሚናዋን ለመወጣት ቁርጠኝነቷን በተደጋጋሚ ገልጻለች። 

የዛሬ 60 ዓመት እ.ኤ.አ ግንቦት 25 ቀን 1963 ለተመሰረተው የአፍሪካ ህብረት መጠናከር ኢትዮጵያ በቁርጠኛ አቋሟ ቀጥላለች።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም