ቀጥታ፡

የግብረገብነትን እሴት ለትውልድ በማስረፅ ኢትዮጵያን በፅኑ መሠረት ላይ መገንባት ይገባናል - የሃይማኖት መምህራንና ምሁራን

አዲስ አበባ ግንቦት 17/2015(ኢዜአ)፦ የግብረገብነትን እሴት ለትውልድ በማስረፅ ኢትዮጵያን በፅኑ መሠረት ላይ የመገንባት ሂደት የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ሲሉ  የሃይማኖት መምህራን እና ምሁራን ገለጹ።

የሃይማኖት መምህራን እና ምሁራኑ ለትውልድ ቀረፃ፣ ለአብሮነትና ለአገር ግንባታ የግብረገብነትን እሴት ማጎልበት የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል። 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የስነ-መለኮትና ስነ-ልቦና መምህር ቆሞስ አባ ጌዲዮን ብርሃነ፤ ግብረገብነትን "የህሊና እና የልቦና ስምምነት፤ የሰውነት ውሃ ልክ መጠበቂያ " ነው ሲሉ ያብራራሉ። 

ግብረገብነት ሰው ከራሱ፣ ከስነ-ፍጥረትና ከፈጣሪ ጋር ሰላም የሚመሰርትበት መሳሪያ መሆኑንም ጠቅሰው፤ የግብረገብነትን እሴት በአግባቡ መጠቀም ይገባል ብለዋል።

በዚህም የማኅበረሰብን አንድነት ማጠናከር፣ የትብብርና አብሮነትን ሰንሰለት ማደርጀት ይገባል ነው ያሉት።

በአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የእስላማዊ ተቋማት የበላይ ኃላፊ ኡስታዝ መሀመድ አባተ፤ ግብረገብነት ሰዎች በዕለት ተለት እንቅስቃሴያቸው ከሌሎች ጋር በሚኖራቸው መስተጋብር የሚያንጸባርቁት መልካም  እሴት መሆኑን አስረድተዋል። 


 

ግብረገብነት በማኅበረሰብ ውስጥ የወል ጥቅምን ሊያስከብሩ የሚችሉ ነገሮች ላይ በማተኮር የጋራ ልዕልናን መሰረት ባደረገ መንገድ የሚተገበር የሥልጣኔ መገለጫ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል። 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የማኅበራዊ ሳይንስ ተመራማሪና መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘላለም ተፈራ፤ የግብረገብነትን ጽንሰ-ሃሳብ ሲያስረዱ ከቤተሰብ ጀምሮ ያሉ ቡድናዊ ስሜቶችን ለበጎ ነገር ለማዋል የሚያግዝ በጊዜ ሂደት የሚገነባ የዕድሜ ልክ ትምህርት ነው ብለዋል።

ነገር ግን ግብረገብነትን በምን ደረጃ ነው እያስተማርን ያለነው? በምን መልኩ ነው ስነ-ምግባርን እየተከልን፣ እየተንከባከብንና እያጸናን ያለነው? የሚለው ጉዳይ በጥልቀት መታየት እንዳለበት አንስተዋል። 

ጠበቃና የሕግ አማካሪው ተዋነይ ሙላቱ በበኩላቸው፤ ግብረገብነት መርህን መሠረት ባደረገ አካሄድ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የማኅበረሰብ ልዕልና መገለጫ የሆነውን ግብረገብነት በትውልዱ ውስጥ በሚገባ ማስረፅ ባለመቻሉ ከግብረገብነት ያፈነገጡ ተግባራት በሁሉም ማዕዘናት እየተስተዋሉ መሆኑን የሃይማኖት መምህራኑና ምሁራኑ ያነሳሉ።

ለዚህ ደግሞ ተቋማት የሚገባቸውን ሥራ አለመሥራት፣ አርዓያ የሚሆኑ ሰዎች አለመበራከት፣ ተቀራርቦ አለመሥራት፣ መገፋፋት፣ የሉላዊነት(ግሎባላይዜሽን) ተፅዕኖዎችና ሌሎችንም በምክንያትነት ያነሳሉ። 

በመሆኑም የግብረገብነትን እሴት የተላበሰ ትውልድ ለመገንባት ልዩነትን የሚያሰፉ አካሄዶችን የማስተካከል ሥራ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ መክረዋል።

የሕግ ሥርዓቶችን መፈተሽ፣ ምክንያታዊነትን ማስቀደም፣ የመረጃና ተግባቦት ሥርዓትን ማስተካከል፣ መደማመጥና መከባበር ወሳኝ መሆኑንም አብራርተዋል። 

የግብረገብነት ጉዳይ ለአንድ ወገን የሚተው ሳይሆን የጋራ ርብርብን የሚጠይቅ በመሆኑ እሴቱን ለትውልድ በማስረጽ ኢትዮጵያን በፅኑ መሠረት ላይ መገንባት ይገባል ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም