የሸገር ከተማን ለአርሶ አደሩና ለከተማ ግብርናም ምቹ የሆነ ከተማ ለማድረግ እየተሰራ ነው - የከተማው ግብርና ጽህፈት ቤት - ኢዜአ አማርኛ
የሸገር ከተማን ለአርሶ አደሩና ለከተማ ግብርናም ምቹ የሆነ ከተማ ለማድረግ እየተሰራ ነው - የከተማው ግብርና ጽህፈት ቤት
ሸገር ግንቦት 16/2015(ኢዜአ): - የሸገር ከተማን ለአርሶ አደሩና ለከተማ ግብርና ምቹ እና ተምሳሌት የሆነ ከተማ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ የከተማው ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።
በከተማ ግብርና እና በተቀናጀ የእርሻ ስራ ላይ ሲሰለጥኑ የነበሩ የከተማዋ ሞዴል አርሶ አደሮች እና የዘርፉ አመራሮች የተሳተፉበት የከተማ ግብርና ጉብኝት በሸገር ከተማ ባሉ ክፍለ ከተሞች ተካሄዷል።
የኢትዮጵያ የአካል ድጋፍ አገልግሎት በገፈርሳ ግቢው እያካሄደ ያለው የተቀናጀ የግብርና ስራ፣ መናገሻ ኢንተግሬቲድ ኦርጋኒክ ፋርም እና በኮሎቦ የሚገኘው የአቶ ጥበበ የወተት ላሞች እርባታ በገፈርሳ ጉጄ ክፍለ ከተማ ከተጎበኙ የግብርና ስራዎች መካከል ይገኛሉ።
የሸገር ከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጫላ አደሬ "ከተማው ካለው ነዋሪ መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው አርሶ አደር ነው"፤ከተማው ዘመናዊ የግብርና አሰራር በመከተልና አርሶ አደሮች ሰርተው ውጤታማ የሚሆኑበት እንዲሆን እየተሰራ ነው ብለዋል።
የጉብኝቱ ዓላማም አርሶ አደሩ በተቀናጀ የግብርና አሰራር ላይ በንድፈ ሀሳብ ሲሰለጥን የቆየውን በተግባር መሬት ላይ በመመልከት በልምዱ ወደ ስራው እንዲገባ ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬ የተጎበኘው የተቀናጀ የግብርና ስራ አመራር በትኩረት ከሰራ ሁሉን ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የገፈርሳ ጉጄ ክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ አቶ አሸናፊ ጨመዳ ናቸው።
ከሸገር ከተማ ምስረታ ዓላማዎች አንዱና ዋነኛው አርሶ አደሮቹን በማቀፍ ለሌላው ተምሳሌት የሚሆንና ግብርና እንዲከናወን ማስቻል መሆኑን አመልክተዋል።
የስልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ዛሬ የተመለከቱት ስራ የበለጠ እንዲሰሩ መነሳሳት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።