ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ የነበራትን ታሪካዊ የመሪነት ሚና አሁንም አፍሪካዊያንን በማስተባበር ልታጠናክረው ይገባል - አምባሳደር ጥሩነህ ዜና

አዲስ አበባ ግንቦት 16/2015(ኢዜአ)፦  ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ የነበራትን ታሪካዊ የመሪነት ሚና በማጎልበት አሁንም አፍሪካዊያንን በማስተባበር ልታጠናክረው ይገባል ሲሉ አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ተናገሩ። 

የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የዛሬው የአፍሪካ ሕብረት ከተመሰረተ ነገ ግንቦት 17 ቀን 2015 ዓ.ም 60ኛ ዓመት ይሞላዋል።

የአሁኑ አፍሪካ ሕብረት የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአፍሪካ አንድነትና ትብብርን ለማጠናከር፣ የአፍሪካ አገራት ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ እንዲሁም የፀረ ቅኝ ግዛት ትግል በማጋጋል ነጻነቷ የተከበረ የአህጉርን ለመፍጠር በማለም ነበር እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1963 የተመሰረተው።
 

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 ኅብረቱ ከተመሰረተ በ50ኛ ዓመቱን ሲያስቆጥር፤ በቀጣይ 50 ዓመታት አህጉሪቷን በምጣኔ ሃብት፣ በፖለቲካና በማህበራዊ እድገት የተሻለ ደረጃ ላይ እንድትደርስ በማለም የ2063 አጀንዳ ተቀርጾ ወደ ትግበራ ተገብቷል። 

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሰረተባትና መቀመጫ ሆና የተመረጠችው ኢትዮጵያም ከድርጅቱ ምስረታ ጥንስስ እስከ ዕውን መሆን አይተኬ ሚና እንደነበራት ዕሙን ነው።

ኢትዮጵያን በመወከል ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና በሌሎች አገራት በአምባሳደርነት ያገለገሉት አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና፤ የአድዋ ድል የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት እርሾ ነበር ይላሉ።

'ኢትዮጵያ በአድዋ ጦርነት ድል ባታደርግ ኖሮ ታሪክ በተቀየረ ነበር' የሚሉት አምባሳደሩ፤ የአድዋ ድል መጎናጸፏ ለአፍሪካዊያንና ለመላው ጥቁሮች ነጻነትና ሉዓላዊነት ትግል ፋና ወጊ አድርጓታል ባይ ናቸው።

የአድዋ ድል አዲስ አበባን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት እንድትታጭ፣ ኢትዮጵያም ለመላው ጭቁን ሕዝቦች የንቅናቄ ተምሳሌት እንድትሆን ያስቻለ ድል ነው ብለዋል። 

የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካ የሚለው እሳቤ እንዲመጣ ቀደምት መሪዎች የቀድሞውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረትና ችግሮቻቸውን በራሳቸው ተቋም እንዲፈቱ የመሪነት ሚና መወጣቷን አውስተዋል።

በሌላ በኩል በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁሮች አማካኝነት የፓን-አፍሪካኒዝም ማበብ ምሳሌ እንደነበረች አንስተዋል።

ይህ  ቀደምት ሚናዋ ዛሬም ልትጠቀምበትና የአፍሪካዊያን ትብብር መጠናከር የመሪንት ሚናዋን ልትወጣ እንደሚገባት ነው አምባሳደር ጥሩነህ የገለጹት።

የፓን አፍሪካዊነት እንቅስቃሴ ጥቁሮች የፈለጉትን በራሳቸው አቅም ማድረግ እንደሚችሉ ያሳየ መሆኑን ገልጸው ዛሬም ይህ አቋም መጠናከር አለበት ብለዋል።

አፍሪካዊያን ለእኩልነትና ለዴሞክራሲ መስፈን ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባም አመልክተዋል።   

የአፍሪካ ሕብረት እንደ ተቋም የመፈጸም አቅሙ እያደገ መምጣቱንም ያስታውሱት አምባሳደሩ ኢትዮጵያም የፓን አፍሪካዊነት ታሪካዊ የመሪነት ሚና ዛሬም ተጠናክሮ መቀጠልም እንዳለበት አንስተዋል።

በተለይም ከሌሎች የውጭ ኃይሎች መፍትሄ ካልመጣ ውጤታማ አይሆንም የሚሉ አካላት ከቀደምት አባቶች እሴትና መርህ ያነፈገጠ እንደሆነ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ አፍሪካዊያን ማስተባበርና መተባበር ቀጣይነት ያለው የዲፕሎማሲ መርህ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

በፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር ግንቦት 1963 በአዲስ አበባ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት የ32 አገራት መሪዎች መታደማቸውን ታሪክ ያስረዳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም