አመራሩ የሕዝብ ፍላጎት ላይ በማተኮር አገርን በብልህነት የመምራት ጥረቱን ሊያጠናከር ይገባል - ዶክተር ምህረት ደበበ - ኢዜአ አማርኛ
አመራሩ የሕዝብ ፍላጎት ላይ በማተኮር አገርን በብልህነት የመምራት ጥረቱን ሊያጠናከር ይገባል - ዶክተር ምህረት ደበበ
አሶሳ ግንቦት 16/ 2015 (ኢዜአ) ፡- አመራሩ መሰረታዊ የሕዝብ ፍላጎት ላይ በማተኮር አገርን በብልህነት የመምራት ጥረቱን ሊያጠናክር እንደሚገባ የአፍሪካ ልህቀት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ምህረት ደበበ ገለጹ።
ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አመራሮች በአሶሳ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
የአፍሪካ ልህቀት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ምህረት ደበበ እንዳሉት፤አመራሮች የሚያከናውኗቸውን ተግባራት ሁሉ ከስሜታዊነት ነጥለው መመልከት አለባቸው፡፡
አመራሩ ሕብረተሰቡን ወርዶ ማዳመጡ ስብዕናው የተሟላ ስሜቱ ያልተሳሳተ እንዲሆን ያደርገዋል ያሉት ይህም የማህበረሰቡን ደስታ፣ ቁጣና ሌሎችንም ስሜቶች በሚገባ መገንዘብ የበለጠ ተቀራርቦ መስራት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
አመራሮች የብዙሃኑን ፍላጎት መረዳት እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብት የሚለማው አመራሩ ዋነኛ የሕዝብ ፍላጎት በሆኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ በማተኮር አገርን በብልህነት የመምራት ጥረቱን ሲያጠናክር ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ።
በዚህ ረገድ አመራሮች የተሻለ የውሳኔ አሰጣጥ ላይ መድረስ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው፤ ክልሉ የበርካታ ተፈጥሮ ሃብት ባለቤት ቢሆንም በሚፈለገው ልክ እንዳልለማ ገልጸዋል፡፡
የሕብረተሰቡን ኑሮ በመቀየር ረገድ ብዙ ስራዎች ይጠብቁናል ያሉት አቶ አሻድሊ፤ የተገኘውን ሰላም በማስቀጠል ከስሜታዊነት በጸዳ መንገድ በመነጋገርና የሰከነ አካሄድ በመከተል በሕብረተሰቡ ሕይወት ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
የክልሉ የአመራሮች ስልጠና እስከ ግንቦት 21 ቀን 2015 ይቆያል።