ማዕከሉ በሽታን በመቋቋም ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ  የዝንጅብል ዝርያዎች ለማውጣት ምርምር እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ

423

ጎንደር፤  ግንቦት 16 ቀን 2015 (ኢዜአ) ፡- የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል በሽታን በመቋቋም ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ   የዝንጅብል ዝርያዎችን ለማውጣት በ36 ዝርያዎች ላይ  ምርምር እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የምርምሩ ስራ በጭልጋ ወረዳ የተከሰተውን የዝንጅብል በሽታ ለመከላከል ዝርያዎችን በአዲስ ለመተካት  መሆኑ ተገልጿል።

የማዕከሉ አስተባባሪ አቶ ምንተስኖት ወርቁ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤  በጭልጋ ወረዳ በተከሰተው በሽታ በሰባት  ቀበሌዎች በዝንጅብል ይለማ የነበረ 300 ሄክታር መሬት ላለፉት አስር ዓመታት ከዝንጅብል ምርት ውጪ ሆኗል።፡

ለበሽታው መከሰተም የአካባቢው አርሶ አደሮች ጥራትና እውቅና የሌላቸው የዝንጅብል ዝርያዎችን በመጠቀማቸው የመጣ ችግር መሆኑን ባካሄዱት ምርምር ማረጋገጣቸውን አስረድተዋል፡፡ 

ይሄን ችግር ለመፍታት በሽታ የመቋቋም አቅም ያላቸውንና ምርታማ የሆኑ የዝንጅብል ዝርያዎችን በምርምር በመለየት ባለፉት አራት ዓመታት የዝርያ  ማሻሻል ስራ  ሲያካሂድ መቆየቱን ገልጸዋል።

ለዚህም ማዕከሉ ለአካባቢው ስነ-ምህዳርና የአየር ንብረት ተስማሚ የሆኑትን 36 የዝንጅብል ዝርያዎች ላይ ምርምር በማካሄድ  በሽታን በመቋቋም ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ 16ቱን በመለየት በቤተ ሙከራ ተጨማሪ ምርምር እያካሄደ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ከአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የቲሹ ካልቸር ምርምር ማዕከል ጋር በመተባበር ከበሽታ የጸዱ ሁለት ዝርያዎችን ለይቶ በማሳደግ ላይ እንደሚገኝ አስተባባሪው ጠቅሰዋል፡፡ 

በቀጣይ በሰርቶ ማሳያና በገበሬ ማሳ ላይ በማላመድና በማስተዋወቅ አርሶ አደሩ ዳግም ወደ ዝንጅብል ማምረት እንዲመለስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በጭልጋ ወረዳ  በዝንጅብል ልማት የተሰማሩ ከአንድ ሺህ በላይ አርሶአደሮች በዓመት ከ84ሺህ ኩንታል በላይ ዝንጅብል አምርተው ለገበያ ያቀርቡ እንደነበር  የተናገሩት የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት አስተባባሪ ወይዘሮ ጸሃይ ዘሩ ናቸው፡፡

አሁን ላይ ግን በዝንጅብል ይለማ የነበረው ከ300 ሄክታር በላይ መሬት ከምርት ውጭ በመሆኑ አርሶ አደሮቹ ከፍተኛ ገቢ ከሚያገኙበት የዝንንጅብል ምርት በመውጣታቸው ገቢያቸው መቀነሱን ገልጸዋል፡፡  

የጎንደር የግብርና ምርምር ማዕከል ችግሩን በመፍታት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ እያደረገ ያለው ጥረት  የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በወረዳው የከንበራ ቀበሌ  አርሶአደር ሲሳይ መኳንንት  በሰጡት አስተያየት፤ በተከሰተው በሽታ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ አለማ የነበረውን የዝንጅብል ምርት በማጥፋቱ ተስፋ ቆርጩ ከዝንጅብል ምርት ወጥቻለሁ ብለዋል፡፡

አሁን ላይ ማዕከሉ በሚያደርገው ምርምር በሽታን የሚቋቋም አዲስ የዝንጅብል ዝርያ ከቀረበላቸው ከፍተኛ ገቢ ወደ ሚያስገኘው የዝንጅብል ልማት ዳግም እንደሚመለሱ ገልጸዋል፡፡

በዚሁ ወረዳ የቤዛዋ ቀበሌ አርሶ አደር በላይ መንግስቱ ፤ በዝንጅብል ከሚያለሙት ሩብ ሄክታር  መሬት 70 ኩንታል ያገኙ እንደነበር አስታውሰው፤   በተከሰተው በሽታ ምክንያት ማምረት እንዳቆሙ ተናግረዋል፡፡

የምርምር ማዕከሉ አዲስ ዝርያ እንዲያቀርብልን በተደጋጋሚ እያሳሳብን እንገኛለን ያሉት አርሶአደሩ፤ ዝንጅብል አምርተው በመሸጥ በሚያገኙት ገቢ ኑሮቸውን ማሻሻል ችለው እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

የዝንጅብል ምርት ለምግብ ማጣፈጫ ለመድሃኒት መቀመሚያና ለመዋቢያ ምርቶች በግብአትነት በስፋት የሚውል የግብርና  ምርት መሆኑ ተመልክቷል።   

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም