አሰሪዎች የተሻሻለውን የግል ድርጅት ሰራተኞች የጡረታ አዋጅ መገንዘብና በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል- የኢትዮጵያ አሰሪ ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
አሰሪዎች የተሻሻለውን የግል ድርጅት ሰራተኞች የጡረታ አዋጅ መገንዘብና በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል- የኢትዮጵያ አሰሪ ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን
አዲስ አበባ ግንቦት 16/2015 (ኢዜአ)፡- አሰሪዎች የተሻሻለውን የግል ድርጅት ሰራተኞች የጡረታ አዋጅ መገንዘብና በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲል የኢትዮጵያ አሰሪ ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን አሳሰበ።
ኮንፌዴሬሽኑ ተሻሽሎ የወጣውን የግል ድርጅት ሰራተኞች የጡረታ አዋጅ ቁጥር 1268/2014 በሚመለከት ለተጠሪ ተቋማቱና ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጅቷል።
በመድረኩ በግል ድርጅት ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር የሕግ አገልግሎት ዳይሬክተር ግርማ ሲሳይ የአዋጁን ይዘትና አተገባበር በሚመለከት ገለጻ አድርገዋል።
አዋጁ ከወጣ ጀምሮ በሁሉም የግል አሰሪ ተቋማት ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ቢሆንም የግንዛቤ ክፍተቶች እንዳሉት ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በተለይም በየጊዜው የሚቋቋሙ አዳዲስ የግል ድርጅቶች አዋጁን በአግባቡ ማስተግበር ላይ ውስንነቶች እንዳሉባቸው አመልክተዋል።
ለጡረታ ማስተግበሪያ የሚውል የሰራተኞችን መረጃ በተሟላ መልኩ አለማቅረብና የጡረታ መዋጮ ወጥ አለማድረግ ዋነኞቹ ክፍተቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የሰራተኞች መረጃ አያያዝ በሚመለከት ወጥነት ያለው አሰራር ባለመዘርጋቱ የሰራተኞችን የተለወጡ መረጃዎችን ማመሳከር ላይ ችግሮች እየገጠመን ነው ብለዋል።
ያም ሆኖ አዋጁ ተግባራዊ መደረጉ በአሰሪና ሰራተኛ በኩል ያለው የስራ ግንኙነት በሕግና መመሪያ እንዲደገፍ ማድረጉን በመልካም ጎኑ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አሰሪ ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ጌታሁን ሁሴን በበኩላቸው በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ ሰራተኞችን ማህበራዊ ዋስትናቸው በተገቢው መልኩ መጠበቅ ይገባል ብለዋል።
ይህንንም በማድረግ በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ ሰራተኞች አበርክቷቸውን ማጉላት ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ለዚህም የግል ድርጅት ሰራተኞች የጡረታ አዋጅ ቁጥር 1268/2014 አሰሪዎች በተገቢው መልኩ ስራ ላይ ሊያውሉት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ጎን ለጎንም የግሉ ዘርፍ በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ነው ኢንጂነር ጌታሁን ያስረዱት።
የግሉ ዘርፍ የሚያበረክተውን አዎንታዊ አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል በዘርፉ የተሰማሩ ሰራተኞች የሙያና የእውቀት ብቃታቸውን ማጎልበት አለባቸው ብለዋል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ እስከ ግንቦት 18 የሚቆይ ሲሆን በአዋጁና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር እንደሚደረግ ተገልጿል።