በምስራቅ አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ ግንቦት 16/2015 (ኢዜአ)፡- በምስራቅ አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመከላከል አገራት ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንዳለባቸው ተጠቆመ።
64ኛው የምስራቅ አፍሪካ የአየር ጠባይ አዝማሚያ ትንተና እና ትንበያ ፎረም ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄዷል።
ፎረሙ በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩትና በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) የአየር ትንበያ ማዕከል ትብብር የተዘጋጀ ነው።
በፎረሙ ላይ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ፣ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ክንፈ ኃይለማርያም እና የኢጋድ አባል ሀገራት ተወካዮች ተገኝተዋል።
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በየጊዜው በድርቅና ጎርፍ አደጋዎች ተጋላጭ ሆኗል።
በመሆኑም የቀጣናው አገራት በአየር ጠባይ አዝማሚያ መረጃ ትንተና እና ትንበያ ያላቸውን አቅም በቴክኖሎጂና በእውቀት ማጎልበት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ይህ እውን እንዲሆን ዓለም አቀፍ አጋር አካላት ትብብርና ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ክንፈ ኃይለማርያም በበኩላቸው፤ ፎረሙ የእርስ በርስ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ከፍተኛ ፋይዳ አለው ብለዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ሊደርሱ የሚችሉ የጎርፍና የድርቅ አደጋዎችን ቅድመ ጥንቃቄና ምላሽ ለመስጠት የሚደረጉ ተግባራት ተሞክሮን ለመቅሰም እንደሚያስችል ጠቅሰዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ወቅቱን የጠበቀና ትክክለኛ የአየር ሁኔታ መረጃዎችን በማሰራጨት በቀጣናው የመሪነት ሚናዋን እየተጫወተች ትገኛለች ነው ያሉት።
የኢጋድ የአየር ጸባይ ትንበያና ትግበራ ማዕከል የትንበያ ባለሙያ አቶ ሁሴን ሰይድ የፎረሙ ዓላማ በመጪው የክረምት ወቅት ስለሚኖረው የአየር ጸባይ ትንበያ የጋራ መረጃ እንዲኖርና አገራት ትንበያውን ተጠቅመው ለሚያጋጥሙ ችግሮች በጋራ የቅደመ መከላከል ስራ እንዲያከናውኑና የተቀናጀ ምላሽ እንዲሰጡ ማስቻል ነው ብለዋል።
በመሆኑም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ መረጃን በመለዋወጥና በዘርፉ ሙያዊ አቅምን በማሳደግ ረገድ ፎረሙ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የአየር ጠባይ አዝማሚያ ትንተና እና ትንበያ ፎረም በዓመት ሶስት ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን በአየር ንብረት ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው የፓናል ውይይቶች የሚደረጉበት ነው።
ፎረሙ የአየር ንብረት ሳይንቲስቶችን፣ ተመራማሪዎችን፣ ቁልፍ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ተጠቃሚዎችን፣ መንግስታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ የልማት አጋሮችን፣ ውሳኔ ሰጪዎችን፣ ሚዲያዎችን እና የሲቪል ማህበረሰብ ባለድርሻ አካላትን በስሩ አቅፏል።
ፎረሙ በአባል አገራቱ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ሊያጋጥሙ የሚችሉ አደጋዎችን በአየር ትንበያ ቅንጅታዊ አሰራር ቀድሞ የመከላከል ስራን እንደሚያግዝም ተጠቁሟል።
64ኛው የምስራቅ አፍሪካ የአየር ጠባይ አዝማሚያ ትንተና እና ትንበያ ፎረም ላለፉት ሁለት ቀናት በባለሙያዎች ደረጃ ሲካሄድ መቆየቱ ይታወቃል።