ቀጥታ፡

የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል-ቱሪዝም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ግንቦት 16/2015(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፉ ለዘላቂ ልማት ግቦች መሳካት ያለውን ሚና ለማሳደግ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር የሚያደርጉትን ተሳትፎ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ገለጹ። 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሀገር ልማት ጥናት ኮሌጅ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር  በመተባበር ያዘጋጁት በዘላቂ ልማት ግቦች አተገባበር፣ፈተናዎችና እድሎች ላይ ያተኮረ ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ደኤታ አቶ ስለሺ ግርማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በርካታ ሀገራት ባላቸው ውስን ሀብት ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት ላይ ውጤታማ ተግባራት እያከናወኑ ነው።  

ኢትዮጵያ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በትምህርት፣ ቴክኖሎጂን ጨምሮ በበርካታ መስኮች የዘላቂ ልማት ግቦችን ማሳካት የሚያስችል እምቅ አቅም እንዳላትም አብራርተዋል።  
 

ይህንን እምቅ ሀብት  በመጠቀም ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በምርምር እና በማማከር ዘርፍ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።   

የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ሚና ያለው የቱሪዝም ዘርፍ በስራ ዕድል ፈጠራና በውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ ለኢኮኖሚው በተሻለ መልኩ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ቱሪዝም ሚኒስቴር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጥናትና ምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ምትኬ ሞላ በበኩላቸው፤  በጉባኤው ዘላቂ የልማት ግቦችን ከማሳካት አኳያ ኢትዮጵያ ያለችበትን ደረጃ በመፈተሽ የቀጣይ ተግባራት ላይ መፍትሔ የሚያመላክት ምክክር እንደሚደረግበት ተናግረዋል።

በዚህም ለፖሊሲ አውጪዎችና ሴክተር መስሪያ ቤቶች ግብዓት የሚሆኑ ምክረ ሀሳቦች ይንሸራሸራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው ያነሱት። 

አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዘላቂ የልማት ግቦች ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ ረገድ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።  

ለዚህም ለየትኛውም የጥናትና ምርምር ጉዳይ በጀት ከመመደቡ በፊት የጥናቱ ትኩረት ዘላቂ የልማት ግቦችን ከግምት ማስገባቱ በቅድመ ሁኔታ እንደሚታይ አስረድተዋል።   
 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሀገር ልማት ጥናት ኮሌጅ ዲን ዶክተር ተስፋዬ ዘለቀ እንደገለጹት፤ ኮሌጁ ባለፉት ዓመታት ሀገራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ጥናትና ምርምሮችን ሲያካሂድ ቆይቷል። 

ኮሌጁ ስርዓተ ጾታ፣ ገጠር ልማት፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ስነ ህዝብ፣ አየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ ሀገራዊ ዕድገትን የሚያፋጥኑ ምክረ ሀሳቦችን በምርምር በማስደገፍ ሲያቀርብ እንደነበርም ነው ያነሱት።

በቀጣይም ሀገራዊ የልማት ተግባራት ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር በተናበበ መልኩ በማሳካት ረገድ በጥናትና ምርምር ለመደገፍ አበክሮ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ዘላቂ የልማት ግቦች ከሚባሉት መካከል ድህነትን ማጥፋት፣ የተሻሻለ የጤና ሥርዓት መዘርጋት፣ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባት፣ የቱሪዝም ሀብቶችን በተቀናጀ መንገድ ለአገር ዕድገት ማዋል ተጠቃሽ ናቸው።     

ዛሬን ጨምሮ ለሦስት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ ላይ የዘላቂ ልማት ግቦች አፈጻጸም ላይ ትኩረት ያደረጉ እና ለውይይት መነሻ የሚሆኑ የጥናት ውጤቶች ቀርበው በስፋት ውይይት እንደሚካሄድባቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም