አዳማን በዲጂታላይዜሽን አገልግሎትና ቴክኖሎጂ ለማዘመን ከዩኒቨርስቲዎች ጋር በትብብር እየተሰራ  ነው - ከተማ አስተዳደሩ

አዳማ ግንቦት 16/2015(ኢዜአ) ... ከተማዋን በዲጂታላይዜሽን አገልግሎትና ቴክኖሎጂ ለማዘመን ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር እየተሰራ  መሆኑን የአዳማ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ ።

12 ግቦችን የያዘና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች የተካተቱበት የከተማዋ የቀጣይ አስር ዓመታት ስትራቴጂክ እቅድ ይፋ ሆኗል።

አስተዳደሩ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ጋር ስማርት አዳማ ፕሮጄክትን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።

የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ በስማርት አዳማ ፕሮጄክት ውጤታማነት ዙሪያ ያስጠናውን ጥናት ለአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ አስረክበዋል።
 

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት በአዳማ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
 

በዚህም በ175 ሄክታር መሬት ላይ ተግባራዊ የሚሆን የስማርት አዳማ ፕሮጄክት ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታላይዜሽን ለመቀየር ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም በመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም፣ በገቢዎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ ንግድና ገበያ ልማትን  ጨምሮ የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት አገልግሎታቸውን ወደ ዲጂታል እየቀየሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም በከተማዋ የሚሰጡ አገልግሎቶችን 80 በመቶ የሚሆነውን ከወረቀት ምልልስና ከሰው ንክኪ ነፃ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን በማከል።

ይኸ ስትራቴጂክ እቅድም ከተማዋ ለህብረተሰቡ ኑሮ አመችና የዘመነች እንድትሆን፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለቱሪዝምና ኮንፈረንስም ተመራጭ ከተማ ለመገንባት የሚያስችሉ ግቦችን በዋናነት ያካተተ ዕቅድ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህም በከተማዋ በሙያና ክሁሎት የዳበረ ማህበረሰብ ለመፍጠር፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ኢንተርፕሩነሮችን በስፋት ለማሳተፍ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ከንቲባው አክለውም የተዘጋጀው ስትራቴጂክ ዕቅድ የስማርት አዳማ ፕሮጄክት ውጤታማ ለማድረግ ቁልፍ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲዎችም የከተማዋ ህብረተሰብ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ማነቆዎችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ችግር ፈች የጥናትና ምርምር ውጤቶችና የመፍትሔ ሃሳቦችን ከማቅረብ ባለፈ የስማርት አዳማ ፕሮጀክት በባለቤትነት እንዲመሩት የተደረገ ስምምነት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የስማርት አዳማ ፕሮጄክት ውጤታማ እንዲሆን በባለቤትነት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተለይም ለፕሮጄክቱ ውጤታማነት ዩኒቨርሲቲው አርክቴክቸሮችና መሃንዲሶችን ያካተተ ቡድን  በማደራጀት ወደ ስራ ማስገባቱን ጠቅሰው በዚህም ቢሮዎችን አደራጅተን ስማርት ማህበረሰብ ለመገንባት ከአስተዳደሩ ጋር እየሰራን ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በከተማዋ የሰው ሃይል አቅም ግንባታና አመራሮች በፕሮጄክቱ ላይ ግልፅ ግንዛቤ አግኝተው ለተፈፃሚነቱ እንዲሰሩ ስልጠና ጭምር እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

በስማርት አዳማ ፕሮጄክት አተገባበርና ቀጣይ ትኩረት ላይ ባለፉት 10 ወራት ያካሄዱትን ጥናት ለከተማዋ አስተዳደር ማስረከባቸውን የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ገረመው ሁሉቃ ናቸው።

በጥናቱ መሰረት በከተማዋ የህብረተሰቡን አገልግሎት ለማሻሻል ዲጂታል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ  ማድረግ መጀመሩ ጥሩ ቢሆንም አሁንም የተጀመሩት የዲጂታላይዜሽን ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በትብብር እንሰራለን ነው ያሉት።

የከተማዋ መሰረተ ልማት ግንባታና የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ የታገዘና ዲጂታል አገልግሎት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።

ሁሉም ተቋማት ወደ ዲጂታል አገልግሎት መግባት አለባቸው ያሉት ዶክተር ገረመው፤ በዚህም የስራ አጥነትን መቀነስ፣ የከተማዋን የገቢ አቅም ይበልጥ ማሳደግ፣ ብልሹ አሰራሮችን ማስወገድ፣ ሰላምና ደህንነትን በአስተማማኝ ደረጃ በማረጋገጥ የዘመነች አዳማን መፍጠር ይቻላል ብለዋል።

ጥናቱ ለከተማዋ ህብረተሰብ የዕለት ተዕለት አገልግሎት የሚሰጡ 13 ተቋማትን ተደራሽ ያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም