ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ "የሰላም ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት" በይፋ ተመሠረተ

አዲስ አበባ ግንቦት 16/2015 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ሰላም ዙሪያ የሚሰሩ 50 ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅቶች "የሰላም ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት" በይፋ መሰረቱ።

የኢትዮጵያ የሰላም ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት ዛሬ ሲመሰረት ሦስት የጠቅላላ ጉባዔ እና ሰባት የቦርድ አባላትን መርጧል።

ኅብረቱ የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ ፍትሕ እንዲሰፍን፣ የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመሥራት ዓላማ አድርጎ የተመሰረተ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በሰላም፣ በዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ግንባታ ላይ በማተኮር ግጭቶችን ቀድሞ መከላከልና ሲፈጠሩም በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ያደርጋል ተብሏል፡፡

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ፤ በሰላም ዙሪያ በጋራ ለመሥራት ኅብረት ለመሰረቱት ድርጅቶች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በዚህ ወቅት ለኢትዮጵያ ከሰላም የሚበልጥ ጉዳይ ስለሌለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር ተቋም እንዲሆን አሳስበዋል፡፡

የሰላም ሚኒስቴር በሰላምና በሀገር ግንባታ ዙሪያ ከኅብረቱ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ 

የኢፌዴሪ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጂማ ዲልቦ፤ ኅብረቱ አገራዊ ምክክር መድረኩንና የሰላም ሂደቱን በማሳካት፣ በማጽናት አዎንታዊ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ልትደርስበት ላለመችው ሀገራዊ ልማት፣ እድገትና ብልጽግና የጎላ አበርክቶ እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ሰላምን ለማስጠበቅ ከፌደራልና የክልል መንግስታት እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የአገርና ሕዝብ ሰላም እንዲከበር የግንዛቤና የንቅናቄ ሥራዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

አገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች ስራ ላይ ማዋል፤ ለሰላም ግንባታ አጋዥ ስትራቴጂዎችን መለየትና መተንተን ከህብረቱ አባላት ይጠበቃል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም