ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

አዲስ አበባ ግንቦት 16/2015(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በመላው አገሪቱ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት በብጹዓን በሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ በአገርና በውጭ ካሉ ተቋማት ጋር የሚሠራ በአገሪቱ መንግሥትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የሚኖረው የሠላም ኮሚቴ ሰይማለች።

በቤተክርስቲያን አባቶች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት የሃይማኖት አባቶቹ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና የአገር ሽማግሌዎች በጋራ ምክክር አድርገዋል፤ ችግሩም በንግግርና በውይይት መፈታቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከግንቦት 1 እስከ 16 ቀን 2015 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየውን የቤተክርስቲያኗ ዓመታዊውን የርክበ-ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ-ጉባዔ መጠናቀቁን አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ስጥተዋል።

በመግለጫቸውም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሰላም ጉልላት እንደመሆኗ ወቅታዊ ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ በመላው አገሪቱ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት በሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ በአገርና በውጭ ካሉ ተቋማት ጋር የሚሠራ በአገሪቱ መንግሥትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የሚኖረው የሠላም ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስ መሠየሙን ገልጸዋል።

በወቅታዊ ችግሮች ምክንያት በመላ አገሪቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች በአጠቃላይ ችግሮቹን በጥናት በመለየት ቤተክርስትያን ልጆቿን በማስተባበር ሁለንተናዊ ሰብአዊ ድጋፍ የማጽናትና የመጎብኘት መርሃግብሮች እንዲደረጉ ቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑንም ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ ቤተ ክርስቲያኗ በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸውና ሰብአዊ ድጋፍ ለሚሹ የማህበረሠብ ክፍሎች የ20 ሚሊየን ብር ድጋፍ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ መወሠኑን ጠቁመዋል።

በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አህጉረ ስብከቶች ተፈጥሮ በነበረው ወቅታዊ ችግር ምክንያት በአህጉረ ስብከትና አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት ስለተቋረጠ በዚሁ መነሻነት ችግሮች እንዲቀረፉና ወደ መደበኛው የአሰራር ስርአት መዋቅር እንዲመለስ 7 ሊቃነ ጳጳሳትን በመሰየም ከፌደራል እና ኦሮሚያ ክልል መንግስት ጋር በመወያያት ችግሮች እንዲፈቱ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አሳልፏል ብለዋል።

ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳትን በተመለከተ ክፍት በሆኑና በተደራራቢነት በተያዙ እንዲሁም ጉልህ እና አንገብጋቢ ችግር ባለባቸው በኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ባሉ አህጉረ ስብከት ላይ 9 ኤጲስ ቆጶሳትን እንዲሾሙ አስመራጭ ኮሚቴ ተሰይሟል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት የሃይማኖት አባቶቹ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና የአገር ሽማግሌዎች በጋራ ምክክር አድርገዋል፤ ችግሩም በንግግርና በውይይት መፈታቱ ይታወሳል።

በውይይታቸውም አንድነትን የሚያፀና እና አገልግሎትን የሚያሰፋ መንገድ መከተል ተገቢ መሆኑን በማመን ከሥምምነት ተደርሷል።

ከቋንቋ ጋር በተገናኘ የሚነሡ ሐሳቦችን ለመመለስ ቤተክርስቲያን የጀመረችውን ሥራ አጠናክራ እንድትቀጥል እንዲሁም በበጀትና በሰው ኃይል ማጠናከር ትኩረት እንዲሠጠው ከሥምምነት መደረሱም ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም