ቀጥታ፡

የሆቴሎች ክፍያ በዲጅታል ሲስተም መሆኑ ለተገልጋዮች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል- ማህበሩ 

አዲስ አበባ ግንቦት 16/2015 (ኢዜአ)፡-የሆቴሎች የአገልግሎት ክፍያ በዲጅታል ሲስተም መሆኑ ለተገልጋዮች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የሆቴልና ቱሪዝም ማርኬት ማህበር ገለጸ።

የዲጂታል ቴክኖሎጂው ከ400 በላይ ባለ ኮኮብ ሆቴሎች ለሚገኙባት ኢትዮጵያ በተለይም ከውጭ የሚመጡ እንግዶች የሚያርፉበትን ሆቴል እንዲመርጡ ከማስቻሉ በተጨማሪ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ እገዛ ያደርጋል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ቱሪዝምና ሆቴሎች ማርኬት ማኅበር ፕሬዝዳንት ጌታቸው አለሙ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የማኅበሩ አባል ሆቴሎች ከተያዘው ወር መጀመሪያ አንስቶ የዲጂታል ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መልዕክት መተላለፉን አስታውቀዋል። 

ማኅበሩ አሁን በያዘው አቋም "አሰራራቸውን ቢቻል ሙሉ ለሙሉ ወደ ዲጂታል ክፍያ ለመቀየር ተነጋግረን ወስነናል" ሲሉ ነው የገለጹት። 

አሁን ላይ አስገዳጅ የሚሆንበት ሁኔታ አንደሌለ የጠቀሱ ሲሆን ይህንን ወደ ፖሊሲ ለማምጣት የመንግስት እገዛ ይፈልጋል ብለዋል። 

የዲጂታል ክፍያ ስርዓቱ ሆቴሎች የሚሰጡት አገልግሎት በተገልጋዮች ዘንድ እርካታ እንዲጨምር ከማድረግ ባሻገር ዓለም የደረሰበትን ፈጣንና ቀልጣፋ አሰራር ለመከተል የሚያስችል ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የዲጂታል ግብይት ስርአቱን በመቀላቀል የኢኮኖሚ ደረጃዋን ከፍ ለማድረግ የያዘችውን ጥረት ያግዛልም ብለዋል።

የሆቴሎች ክፍያ በዲጅታል ሲስተም መሆኑ ለተገልጋዮች ምቹና የተቀላጠፈ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ ለውጭ አገር ጎብኝዎችን ቆይታና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የላቀ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
 

የጎልድን ፓርክ ባለቤት እና ስራ አስኪያጅ አቶ ጸጋዬ ተሰማ እና የአይቪዩ ሆቴል ሱፐርቫይዘር ማርታ ገብረማርያም፤ የዲጂታል ክፍያ ስርአት የሆቴሎቹን አሰራር ቀልጣፋና ተወዳዳሪ ያደርጋል ብለዋል።
​​​​​​​

ሆቴሎቹ የዲጂታል ክፍያ ስርአቱን አስቀድመው መጀመራቸውን በማስታወስ ደንበኞችም በሚሰጡት አገልግሎት ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸውልናል ብለዋል።

የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ስርአቱ አገሪቷ ከውጭ እንግዶች የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ የሚያስችል ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ እንግዶች በዲጂታል ክፍያ የሚፈጽሙበት አሰራር ሲተገበር የቆየ ሲሆን ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት የእጅ በእጅ ክፍያዎችን ወደ ዲጂታል ለመቀየር ታስቦ የሚተገበር እንደሆነ ማህበሩ አስታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም