ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት 2 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር ግብይት ተፈጽሟል- አቶ አቤ ሳኖ

አዲስ አበባ ግንቦት 16/2015 (ኢዜአ)፡-ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት 2 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር ግብይት ወይም የገንዘብ ዝውውር መፈፀሙን የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ገለጹ።

መንግስት በ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅዱ እና በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሩ ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

በዚህ ሂደት የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎቶቻቸውን ወደ ዲጂታል አሰራር እየቀየሩ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከወረቀት የፀዳ አገልግሎትና ዲጂታል ኢኮኖሚ እየተገነባ መሆኑን በማንሳት ኢትዮጵያም ወደ ዚህ ምዕራፍ እየተሸጋገረች መሆኗ ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል።

የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቶች በጥሬ ገንዘብ ወይም በወረቀት የሚካሄዱ ግብይቶችን  ከማስቀረት ባለፈ ለደንበኞች ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎትን እንደሚያመጡ ተናግረዋል።

የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን ውጤታማ በማድረግ ሂደትም ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ አሻራውን ለማሳረፍ ከሞባይል ባንኪንግ ጀምሮ ደንበኞች አገልግሎቶችን በዲጂታል መንገድ እንዲያሳልጡ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የዲጂታል ግብይት የገንዘብ ዝውውርን በቀላሉ ለመመዝገብ፣ ለማስተዳደር፣ መልሶ ለማየትና ለማረጋገጥ፣ መረጃ አሰባስቦ ለመተንተንና ውሳኔ ለመስጠት አመቺ ነው ብለዋል።

ባንኩ የሞባይል ባንኪንግ፣ የኢንተርኔት ባንኪንግ፣ የሞባይል ዋሌት፣ የኤቲኤም፣ የፖስ ማሽንና ሌሎችም የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቶችን ወደ ተግባር በማስገባት የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታውን እያገዘ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በዚህም ከ2014 ግንቦት እስከ 2015 ሚያዚያ መጨረሻ ድረስ በሁሉም የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቶች የተከናወነው የገንዘበ ዝውውርና ግብይት 2 ነጥብ 6 ትሪሊዮን መድረሱን ጠቅሰዋል።

በዘንድሮው በጀት ዓመት ያለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ደግሞ 2 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር ግብይት መፈጸሙን አንስተዋል።

የባንኩ ያሉት አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር በአሁኑ ወቅት 42 ሚሊዮን ገደማ መድረሱን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤  30 ሚሊዮኑ የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው ብለዋል።

ከዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት ደንበኞች መካከል 20 ሚሊዮኑ በየጊዜው ሂሳባቸውን እያንቀሳቀሱ መሆኑን አረጋግጠናል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ ሀብቱ 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር መድረሱንም የባንኩ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም