ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ214 ሺህ ቶን በላይ ዓሳ ማምረት የሚያስችል ስራ እየተከናወነ ነው - ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ግንቦት 16/2015(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ214 ሺህ ቶን በላይ ዓሳ ማምረት የሚያስችል ስራ እየተከናወነ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በሁሉም ስነ-ምህዳር በቀላሉ ተመርቶ ከፍተኛ ጥቅም በሚያስገኘው የውሃ ግብርና ዘርፍ ባለሃብቶች እንዲሰማሩም ተጠይቋል።

የዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት(ፋኦ) እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2020 ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም ላይ በውሃ ግብርና ወደ 123 ሚሊዮን ቶን የዓሳ ምርት የተሰበሰበ ሲሆን፤ በገንዘብ ሲሰላ 282 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ይደርሳል ማለት ነው፡፡ 

በኢትዮጵያም ምግብን በጓሮ በማምረት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እስከ 2018 ዓ.ም የሚቆይ "የሌማት ትሩፋት" መርሐ-ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ማስጀመራቸው ይታወቃል፡፡

በሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር ከታቀፉት የግብርና ስራዎች መካከል የውሃ ግብርና በተለይም የዓሳ ምርት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።

በግብርና ሚኒስቴር የዓሳ ሀብት ልማት ዴስክ መሪ ዶክተር ፋሲል ዳዊት፤ አኳካልቸር በተለምዶ ከዓሳ ጋር ይያያዝ እንጂ አልጌ፣ የባህር ውስጥ ተክሎች እንዲሁም 'ክሩስቴሽያን' እና 'ሞሉስክ' ጨምሮ ሌሎች የጀርባ አጥንት የሌላቸው ጥቃቅን እንስሳትን የሚያካትት መሆኑን ይገልጻሉ። 

ኢትዮጵያ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና ሌሎች በቅርብ የተገነቡ ግድቦችን ሳይጨምር በዓመት 94 ሺህ ቶን ዓሳ ማምረት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።

የውሃ ግብርና ውስን ሀብትና ገንዘብ በማንኛውም የውሃ ስነ-ምህዳር ማምረት የሚቻል ቢሆንም ከዓሳ ምርት ውጭ ትኩረት ተሰጥቶ አልተሰራበትም ብለዋል።

በተለይም አልጌ በቀላሉ የሚመረት ለምግብነት የሚውል ከፍተኛ ይዘት ያለውና ለመድኃኒትነት የሚያገለግል ቢሆንም እምብዛም አልተሰራበትም ነው ያሉት ዶክተር ፋሲል።

በሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር የውሃ ግብርናን በተለይ ዓሳና አልጌን በስፋት በማምረት የስራ ዕድል ለመፍጠር፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ገቢ ለማመንጨት በመንግስት በኩል በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ለሁሉም ስነ-ምህዳር ተስማሚ የሆኑ የዓሳ ዝርያዎች እንዳሉ ገልጸው፤ እንደ አገር በ1 ሚሊየን ስኩዌር ሜትር ቦታ ላይ ዓሳ ማምረት ይቻላል ብለዋል፡፡

አምራቾችና የግል ባለሃብቶችን ጭምር በማሳተፍ እስከ 2018 ባሉ ሶስት ዓመታት በየዓመቱ 214 ሺህ ቶን ዓሳ ለማምረት ዕቅድ መያዙን ጠቁመዋል። 

የውሃ ግብርና እንደ ዶሮ፣አትክልትና ፍራፍሬ ያሉ ምርቶችን ጎን ለጎን ማምረት የሚያስችል ቀላል እንዲሁም ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑን ገልጸዋል። 

ዓሳ ከተመረተ በኋላ ለምግብነት የሚውለው ከተረፈ ምርቱ ሲለይ እስከ 70 በመቶ የሚደርስ ሲሆን፤ ለአብነት የዶሮ 48 በመቶ፣ አሳማ፣ በግና ፍየል ደግሞ ከ30 በመቶ አይበልጥም ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለይም በአርሶ አደሩ ዘንድ ገቢራዊ የሚደረገው የዓሳ አመራረት ዘዴ ምንም እንክብካቤ ሳያደርጉ ውሃና ዓሳን በማገናኘት ብቻ የማምረት ሂደት መሆኑን ነው ዶክተር ፋሲል ያስረዱት።

በሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር የአርሶ አደሩንም ሆነ በዘርፉ የሚሳተፉ ባለሃብቶችን በከፊልና ሙሉ በሙሉ በመንከባከብ ሂደት የማምረት ስልት እንዲከተሉ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ባለሃብቶች ለውሃ ግብርና ያለውን ምቹ ስነ-ምህዳር እና የዓሳ ዝርያ በመጠቀም ገቢያቸውን ማሳደግና ኢኮኖሚውን መደገፍ የሚችሉበትን እድል እንዲጠቀሙም ዶክተር ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም