በመጪው መስከረም በፊንላንድ በሚካሄደው ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ ስምንት ስፖርተኞች ይሳተፋሉ

443

አዲስ አበባ ግንቦት 16/2015(ኢዜአ)፡-በመጪው መስከረም በፊንላንድ ታምፔሬ በሚካሄደው ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክለው ስምንት ስፖርተኞች እንደሚሳተፉ የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ አሶሴሽን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ አሶሴሽን ፕሬዝዳንት ኢንስትራክተር ጌታቸው ሺፈራው ለኢዜአ እንደገለጹት ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ስፖርት በኢትዮጵያ መዘውተር የጀመረው ከ1980ዎቹ ወዲህ መሆኑን  ይናገራሉ።

ስፖርቱ በወቅቱ ከኮሪያ ሀገር ልምድ በቀሰሙ የፖሊስ ሰራዊት አባላት እንደተጀመረ አስታውሰው ፤በጊዜ ሂደት ስፖርቱ ከፖሊስ አባላት ውጭ በሌላው የማህበረሰብ አባላት እየተዘወተረና እየተስፋፋ እንደመጣ ተናግረዋል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ ከ250 በላይ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ስፖርት ክለባት መኖራቸውንና በእያንዳንዱ ክለብ  ከ25 እስከ 30 ሰልጣኞች እንደሚሳተፉም ነው የገለጹት፡፡

ስፖርቱ ጤናማ አካልን በማጎናጸፍ ፣ጤናን በመጠበቅና ማህበራዊ ግንኙነትን ማጎልበትን ጨምሮ በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት ነው የተናገሩት።

በተጨማሪ ስፖርቱ ዓለም አቀፍ ውድድር ስፖርት እንደመሆኑ መጠን አሶሴሽኑ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ስፖርተኞችን እንደሚያሳትፍ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከተሳተፈችባቸው የተለያዩ ውድድሮች መካከል ከሶስት ዓመት በፊት በአፍሪካ ደረጃ በታንዛኒያ በተደረገ ውድድር የአንደኝነት ደረጃ ይዛ ማጠናቀቋን አስታውሰዋል።

በመጪው ዓመት መስከረም ወር በፊንላንድ ቴምፔሬ በሚካሄደው ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ተሳታፊ እንደምትሆን ገልጸዋል።

በውድድሩ የሚካፈሉ የብሔራዊ ቡድን አባላት ምርጫ በሚያዚያ ወር በአዲስ አበባ በተካሄደው ሀገር አቀፍ የክለቦች ሻምፒዮና መካሄዱንም አብራርተዋል፡፡

በዚህም  ስምንት ተወዳዳሪዎች መመረጣቸውን ጠቅሰው፤ ከሚቀጥለው ሳምንት በኋላ ልምምድ  እንደሚጀምሩ ተናግረዋል፡፡

በኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ስፖርት በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የማስተር ማዕረግ ያገኙት ማስተር ወጋየሁ በሃይሉ ከብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኛች መካከል አንዱ ሲሆኑ፤ ቡድኑ ጠንካራ ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያስችሉ ስራዎች እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ስፖርት 60 ኢንስትራክተሮችና አንድ ማስተርነት ደረጃ የደረሰ  ባለሙያዎች እንዳሏት ጠቅሰው፤ ይህም ከአፍሪካ የተሻሉ ባለሙያዎች እንዲኖራት ማድረጉን ተናግረዋል

በሻምፒዮናው መሳተፍ ልምድና ተሞክሮ ለመቅሰምና ስፖርቱን የበለጠ ለማሳደግ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በማስታወስ ፤ብሔራዊ ቡድኑ ውጤታማ እንዲሆን አጋር አካላት የሚጠበቅባቸውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም