የግብርናን ጨምሮ ሌሎች ልዩ ልዩ ምርቶች እንደ አዕምሯዊ ንብረት የሚጠበቁበትን ስርዓት መፍጠር ያስችላል የተባለ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

170

አዲስ አበባ ግንቦት 16/2015(ኢዜአ)፡-የግብርናን ጨምሮ ሌሎች ልዩ ልዩ ምርቶች እንደ አዕምሯዊ ንብረት የሚጠበቁበትን የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት የሚያስችል ፕሮጀክት ዛሬ ይፋ ሆኗል።

ለሶስት ዓመት የሚተገበረው ፕሮጀክት ወጪ በፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ እንደሚሸፈን ተገልጿል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ያሏትን ታዋቂ የግብርና ምርቶች በአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ለማስጠበቅ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።


 

ከሕግ ማዕቀፉም ጎን ለጎን ከኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች አንዱና ዋንኛ የሆነውን የቡና ምርት ላይ የተለየ ትኩረት መሰጠቱን አድንቀዋል።

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን የማህበረሰብ ዕውቀት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ታደሰ ወርቁ በበኩላቸው የሕግ ማዕቀፉን የያዘው ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ውስጥ በቦታ ስም ለሚገለጹ ምርቶች አዕምሯዊ መብት ጥበቃ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ይህም ምርቶችን የሚያመርቱ አካላትን ተወዳዳሪ ለማድረግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ መልከዐ ምድርን የሚያመላክት የሕግ ማዕቀፍና የአሰራር ስርዓት እንዲዘረጋ የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።

በመሆኑም አዋጅና ደንብ በማዘጋጀት የንግድ ምልክቶችን ባለቤትነት ለማስጠበቅ ከተሞከሩ ሂደቶች በተጨማሪ በቦታ ጥራታቸው የሚጠቀሱ ልዩ ልዩ ምርቶችን እንደ አዕምሯዊ ንብረት የሚጠበቁበትን ስርዓት ለመፍጠር ፕሮጀክቱ ወሳኝ ጠቃሜታ አለው ነው ያሉት አቶ ታደሰ።

ኢትዮጵያ ውስጥ የግብርና ምርቶች ዋንኛ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ በመሆናቸው ፕሮጀክቱ የግብርና ምርትን የሚያመርቱ አምራቾች የግብይት ሰንሰለት ውስጥ በመግባት ፍትሐዊ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና ከምርቶች የሚገኘውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በአግባቡ እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።

በተጨማሪም በዘርፉ ያሉ ክፍተቶችን በማየትም የአቅም ግንባታ ስራዎችን ለማከናወንና የምርቶች መጭበርበር ተከስቶ ተጠቃሚዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል እንደሚያስችልም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም