64ኛው የምስራቅ አፍሪካ የአየር ጠባይ አዝማሚያ ትንተና እና ትንበያ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 16/2015(ኢዜአ)፡-  64ኛው የምስራቅ አፍሪካ የአየር ጠባይ አዝማሚያ ትንተና እና ትንበያ ፎረም በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።


ፎረሙን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የአየር ትንበያ ማዕከል ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።



በፎረሙ መክፈቻ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ፣የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር  ክንፈ ኃይለማርያምን ጨምሮ የኢጋድ አባል አገራትና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።


በዓመት ሶስት ጊዜ የሚካሄደው ፎረም በአየር ንብረት ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎች የፓናል ውይይቶች የሚካሄዱበት መድረክ ነው።


ፎረሙ የአየር ንብረት ሳይንቲስቶችን፣ተመራማሪዎችን፣የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ተጠቃሚዎችን፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣የልማት አጋሮችን፣ ውሳኔ ሰጪዎችን፣ መገናኛ ብዙሃን እና የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት በስሩ አቅፎ የያዘ ነው።


ፎረሙ በአባል አገራቱ በአየር ንብረት ሳቢያ ሊያጋጥሙ የሚችሉ አደጋዎችን በአየር ትንበያ ቅንጅታዊ አሰራር ቀድሞ የመከላከል ስራ ለመስራት እንደሚያግዝ ተገልጿል።


ላለፉት ሁለት ቀናት በባለሙያዎች ደረጃ ሲካሄድ የቆየው 64ኛው የምስራቅ አፍሪካ የአየር ጠባይ አዝማሚያ ትንተና እና ትንበያ ፎረም ዛሬ በከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ውይይት ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም