ቀጥታ፡

በአየር መንገዱ የሽያጭ ማዕከል ከቀረጥ ነጻ የሚሸጡ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች የቆዳ ኤክስፖርት መዳረሻ አገራትን በማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል- አቶ መላኩ አለበል

 

አዲስ አበባ ግንቦት 16/2015 (ኢዜአ)፡- በአየር መንገዱ የሽያጭ ማዕከል ከቀረጥ ነጻ የሚሸጡ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች የቆዳ ኤክስፖርት መዳረሻ አገራትን በማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር  አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ጋር በአየር መንገዱ ከቀረጥ ነጻ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች የሽያጭ ማዕከል እንቅስቃሴና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ቆዳና ቆዳ ውጤቶች የቀረጥ ነጻ የሽያጭ ማዕከል አፈጻጸም፣ የአገር ውስጥ የቆዳና ምርቶችን ከማስተዋወቅ፣ የምርት ጥራት እና ተደራሽነትን ማስፋፋት ፣አየር መንገዱ ለተለያዩ አገልግሎት የሚያውላቸውንና ሌሎች ከውጪ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች መተካት የሚቻልባቸውና የውጭ ምንዛሬ የገቢ መጠን ማሳደግ የተመለከቱ ጉዳዮች ተነስተዋል፡

የቆዳና ቆዳ ውጤቶች የቀረጥ ነጻ የንግድ ማዕከል ወደ ስራ ከገባ ጀምሮ በምርት ጥራት ፣በገቢ እድገት መጠን፣ የመዳረሻ ገበያ ከማሳደግ፣የአገር ውስጥ ምርቶችን ከማስተዋወቅና ለዜጎች ተጨማሪ የስራ እድልን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገና አበረታች ውጤቶችን እያመጣ እንደሚገኝ የኢንዱትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገልጸዋል፡፡

እንደ አገር የቆዳ ኢንዱስትሪው ከተጋረጠበት አደጋ ለመታደግ ከተሰሩ ስራዎች አንዱ የሆነው የሽያጭ ማዕከሉ ወደ እንቅስቃሴ ከገባበት ጊዜ አንስቶ በተቋም ደረጃ አስፈላጊውን ድጋፍ እየተደረገለት መሆኑን አመልክተዋል።

የታየውን አበረታች ውጤት ተከትሎ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር በዘርፉ ለተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ አምራቾች ተጨማሪ የማምረቻ ቦታዎች የማመቻቸት ስራ መሰራቱን ነው የተናገሩት።

ከቆዳ እና ቆዳ ውጤቶች በተጨማሪም ሌሎች የአገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በዓለም አቀፍ ገበያ እንዲገቡ የማድረግ ስራዎችን ለማከናወን ከአየር መንገዱ ጋር መስማማታቸውን አቶ መላኩ በውይይታቸው ላይ አንስተዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በኢትዮጵያ የተመረቱ ምርቶች ለዓለም አቀፍ ገበያ ተደራሽ በማድረግ የውጪ ምንዛሬ የገቢ መጠንን ለማሳደግ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም  አስታውቋል።

አየር መንገዱ የቆዳ ኢንዱስትሪውን ለማዳን እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ አስፈላጊውን ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱንና በዚህም ከቀረጥ ነጻ የሽያጭ ማዕከል በማመቻቸት ግብይት እየተከናወነ መሆኑን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገልጸዋል።

በዚህ ረገድም አየር መንገዱ ጥራት እና ቀጣይነት ያለው የምርት አቅርቦት ማቅረብ ለሚችሉ አምራቾች ከውጪ ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባቸውን የምግብ ነክ ምርቶችንና የስራ አልባሳትን በአገር ውስጥ ለመተካት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ዋና ስራ አስፈጻሚው መግለጻቸውን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም