ቀጥታ፡

በዞኑ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለአንድ ወር በተካሄደ የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ ከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

አምቦ ግንቦት16/2015 (ኢዜአ)፡-በምዕራብ ሸዋ ዞን በብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ አስተባባሪነት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለአንድ ወር በተካሄደ የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ ከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ።

የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ ኃላፊ ወይዘሮ ታደለች አብዲሳ እንደተናገሩት በዞኑ ከተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች በአንድ ወር 6 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዶ ሲሰራ ቆይቷል።

በዚህም በቦንድ ግዢ እና በስጦታ መልክ ለመሰብሰብ ከታቀደው ውስጥ 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ እንደተቻለም ገልጸዋል።

በተለይም የዞኑ ሴቶች አደረጃጀቶች ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ገልጸው ከዚህ ቀደምም ለግድቡ ግንባታ በቦንድ ግዢና በስጦታ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ንቅናቄው የተካሄደው ከሚያዚያ 15 እስከ ግንቦት 15 ቀን 2015 ድረስ መሆኑን አስታውሰዋል።

ለኢዜአ አስትያየታቸውን የሰጡ የዞኑ የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች በበኩላቸው ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬታማነት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

በንግድ ስራ የሚተዳደሩት የቶኬ ኩታዬ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ አቦነሽ መንግስቱ የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ሲደግፉ መቆየታቸውን ይናገራሉ።

ለግድቡ ግንባታ ስኬት እስካሁን የ50 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ጠቁመው ግድቡ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት እስኪሰጥ ድረስ ድጋፋቻውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

በጨርቃጨርቅ ንግድ የተሰማሩት አቶ መሃመድ የሱፍም እንዲሁ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የቦንድ ግዢ ከተጀመረ አንስቶ 80 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል።

ግድቡ ያለበት ሁኔታ ስላስደሰታቸው ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ቃል ገብተዋል፡፡

በምእራብ ሸዋ ዞን የግድቡ መሰረት ከተጣለበት ቀን ጀምሮ በዞኑ ከመንግስት ሰራተኞች፣ ከባለሀብቶች፣ ከአርሶ አደሮችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በቦንድ ግዢና በስጦታ 125 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡ ይታወሳል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም