በባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ልማት አርሶ አደሩን የታዳሽ ኃይል እና ተፈጥሮ ማዳበሪያ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተደረገ ነው - የኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ

አዲስ አበባ ግንቦት 15/2015(ኢዜአ)፡-በባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ልማት አርሶ አደሩን የታዳሽ ኃይል እና ተፈጥሮ ማዳበሪያ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ገለጸ።

በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ሸዋ ዞን በወልመራ ወረዳ በኢትዮጵያ መንግስት እና በአውሮፓ ህብረት ትብብር የተገነባ "የጋባ ሮቢ ሞዴል ባዮጋዝ መንደር" ፕሮጀክት ተመርቋል።

በምርቃቱም የፌደራል፣ የክልል መንግስታት የስራ ኃላፊዎች፣ የአውሮፓ ህብረት ተወካዮች ጨምሮ የዞንና የወረዳ የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር መሀመድ ዚያድ፤ በክልሉ ከፌደራልና ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ልማት የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ አቅም ያላቸው ወረዳዎች በማተኮር የአርሶ አደሩ የኃይል አማራጭ ባሻገር የአፈር ለምነትን በመመለስ ምርታማነቱን እንዲያሳደግ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ወደ 10 ሺህ የሚጠጋ የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ልማት መከናወኑን ገልጸው፤ በቀጣይም ይህ ስራ ተጠናክሮ  እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብሔራዊ ባዮ ጋዝ ፕሮግራም ኃላፊ አቶ ተመስገን ተፈራ፤ የባዮ ጋዝ ልማት  በተለያዩ ክልሎች ለኃይል አማራጭ እና ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል ብለዋል።

10 ዓመታትን ባስቆጠረው የባዮ ጋዝ ልማት ፕሮግራም ትግበራ አርሶ አደሮችን በኤሌክትሪክ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ፣ በስራ እድል ፈጠራ እና በአካባቢ ጥበቃ ስራ ተጠቃሚ መሆናቸውንም ነው ያነሱት።

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኤሊያስ ከድር የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ አርሶ አደሩን በተፈጥሮ ማዳበሪያ በማስጠቀም በአሲዳማና ጨዋማነት የተጠቃን አፈር ለምነት እንዲመለስ አስችሏል ብለዋል።

የሞዴል የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ መንደሮችን በማስፋትም አርሶ አደሩን በኃይል አማራጭ አቅርቦት እና በአፈር ለምነት ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል። 

የአውሮፓ ህብረት የኢኮኖሚ እና መሰረተ ልማት ቡድን መሪዋ ሳኔ ዊሊያም ህብረቱ የአርሶ አደሮችን የኃይል አማራጭ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም